ፓርቲዎች በ160 የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታ አቅርበዋል- ምርጫ ቦርድ
ፓርቲዎች የሚያቀርቡት አቤቱታዎች ታይተው ተቀባይነት ካላቸው ድጋሚ ምርጫ ሊደረግ ይችላል
ችግር የሌለባቸውና ህጉ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች ያሟሉ የምርጫ ክልሎች ውጤት ይፋ ማድረግ ተጀምሯል
ፓርቲዎች በ160 የምርጫ ክልሎች ላይ ቅሬታ መቅረቡን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአንዳንድ ክልሎች ላይ በበርካታ ፓርቲዎች ቅሬታ መቅረቡን አስታውቀዋል።
“ከዚህ ጋር በተያያዘ በእነዚህ የምርጫ ክልሎች የምርጫውን ውጤት እንዳናወጣ አድርጎናል” ያሉ ሲሆን፤ “የምርጫ ውጤት የሚለውጥ ከሆነ እያየን ነው” ብለዋል።
“ፓርቲዎች አቤቱታዎች በተበታተነ መልክ ነው ያቀረቡት” ያሉት ሰብሳቢዋ፤ ዛሬ ከፓርቲዎች ጋር አቤቱታ ምን መያዝ አለበት የሚለው ላይ ሰፊ ውይይት መደረጉን በመግለጽ፤ ቦርዱም የህግ እገዛ ሊያደርግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።
አቤቱታዎቻው ታይቶ ተቀባይነት ካላቸው ድጋሚ ምርጫ ለማድረግ፤ ተቀባይነት ከሌለው ደግሞ ውጤት የሚገለጽ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ቦርዱ ከነገ ጀምሮ አቤቱታዎቻቸውን ማየት እንደሚጀምር ያሳወቁት ሰብሳቢዋ፤ “የቦርዱ ውሳኔ ያላረካው ካለ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ይችላል” ብለዋል።
ቦርዱ ችግር የሌለባቸው እና ህጉ የሚጠይቃቸውን መስፈርቶች በሙሉ ያሟላ ውጤት ከዛሬ ጀምሮ ይፋ እንደሚደረጉም አስታውቀዋል።
በጊዜያዊነት የሚለቀቁ የምርጫ ውጤቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉም በመግለጽ፤ ከባድ የሆነ አቤቱታ ያልቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች ውጤት ነው የሚለቀቀው ብለዋል።
በሁሉም የምርጫ ክልሎች ህጉ በሚጠይቀው መሰረት ይፋ ለማደረግ እየተሰራ መሆኑንም አሳውቀዋል።