ፓርቲው ጉባኤውን ከመጥራቱ በፊት የጉባኤ አጠራር ዝርዝር ዕቅዱን እንዲያቀርብ መወሰኑንም ቦርዱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንደሚገባው አስታወቀ፡፡
ሆኖም ፓርቲው ከአሁን ቀደም ከተስተዋሉበት የአሰራር ችግሮች አንጻር ከጉባኤው በፊት የጉባኤውን አጠራር ደንብ እና አጠራሩ የምርጫ ህጉን የተከተለ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያለው ቦርዱ የጉባኤ አጠራሩ ዝርዝር ዕቅድ እንዲቀርብለት ወስኗል፡፡
በውሳኔው መሰረትም ዝርዝር ዕቅዱ፣ የጉባኤውን አጠራር በተለከተ በተገቢው የፓርቲው አካል የተሰጠ ውሳኔ እና የውሳኔው ቃለ ጉባኤዎች በአንድ ወር ጊዜ ውሰጥ ማለትም እስከ ሚያዚያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀርቡለት ጠይቋል።
ቦርዱ በፓርቲው አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ መተላለፍ አለመተላለፉን፣ ውሳኔው በደንቡ መሰረት መሆን አለመሆኑን፣ ደንቡን ያልተከተለ ከሆነ ምከንያቱ ምን እንደሆነ እንዲሁም ተጠሪ ለአመልካች ያቀረበው ሰነድ የተሟላ መሆን አለመሆኑ በጭብጥነት ይዞ ከህግ እና መተዳደሪያ ደንቡ አንጻር አጣርቶ እንዲወስን በፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠውን ትዕዛዝ አስመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ መስጠቱን ዛሬ ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ የባለሙያዎች ቡድን በማዋቀርና በሰበር ሰሚው በተሰጡ ትዕዛዞች መሰረት ጉዳዩን በመርመር የተሰጠ ነው እንደ ቦርዱ ገለጻ፡፡
ጠቅላላ ጉባኤው በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ስልጣን ባለው አካል ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ አለመጠራቱን በድጋሚ አረጋግጦ ቀደም ሲል መጋቢት 04 ቀን 2013 ዓ.ም የሰጠውን ውሳኔ ያጸናው የባለሙያዎች ቡድኑ ቦርዱ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት ሊጫወት የሚችለውን ሚና እንደገና እንዲያየው በሰበር ሰሚ ችሎቱ የቀረበለትን ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁለት አማራጭ የውሳኔ ሀሳቦችን አቅርቧል፡፡
የውሳኔ ሃሳቦቹ ፓርቲው በመተዳደሪያ ደንቡ በተጠቀሱ አዋጆች መሰረት ትክክለኛና ህጋዊ ሂደቱን ጠብቆ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂድ እና ቦርዱ የፓርቲውን ውሳኔ የማስተላለፍ መብት ሳይነካ የፓርቲውን የውስጥ ህግ በመከተል ለተፈጠሩት ችግሮች መፍትሄ ያፈላልግ የሚሉ ናቸው፡፡
ሁለተኛው አማራጭ ቦርዱ ጠቅላላ ጉባኤ የመጥራት ስልጣን ያለውን የፓርቲውን ብሔራዊ ምክር ቤት 48 አባላት በአድራሻቸው ፈልጎ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራበትን ሁኔታ እንዲያመቻች እድል ይሰጣል፡፡
ሆኖም የፓርቲውን የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት በአድራሻቸው የስብሰባ ጥሪ እንዲደርሳቸው በማድረግ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ማድረግ ሊፈጸም የማይቻል ሆኖ ማግኘቱን ቦርዱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በመሆኑም በቡድኑ የቀረበውን ሌላኛውን የውሳኔ ሃሳብ እንደ አማራጭ በመውሰድ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት እንደሚገባው ገልጿል፡፡
ነገር ግን ፓርቲው ካሉበት የአሰራር ችግሮች አንጻር ከጉባኤው በፊት የጉባኤው አጠራር ደንቡን እና የምርጫ ህጉን የተከተለ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብሏል፡፡
በመሆኑም የጉባኤ አጠራር ዝርዝር ዕቅድ፣ የጉባኤውን አጠራር በተመለከተ በተገቢው የፓርቲው አካል የተሰጠ ውሳኔ እና የውሳኔው ቃለ ጉባኤዎች ይህን ውሳኔ ባሳወቀ በአንድ ወር ጊዜ ውሰጥ ማለትም እስከ ሚያዚያ 6 ቀን 2014 ዓ.ም እንዲቀርቡለት መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል።