መራጮች እስከ ቀጣዩ ሳምንት አርብ ድረስ መመዝገብ እንደሚችሉ ቦርዱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመራጮች ምዝገባ ቀንን በድጋሚ ለ1 ሳምንት ማራዘሙን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ መራጮች እስከ ቀጣዩ ሳምንት አርብ ድረስ መመዝገብ እንደሚችሉ ምዝገባውን አስመልክቶ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በመጀመሪያ ሰሞን የነበረው የመራጮች ምዝገባ መቀዛቀዝ ተስተውሎበት ነበር ያለው ቦርዱ ሁኔታው በከፍተኛ ሁኔታ ተሻሽሎ በአሁኑ ወቅት በጊዜያዊነት በተሰበሰበው መረጃ (ያለፉት ሶስት ቀናትን ሳይጨምር) 28 ሚሊዬን 731 ሺ 935 ያህል መራጮች መመዝገባቸውን ገልጿል፡፡
ምዝገባው በ41 ሺ 798 ምርጫ ጣቢያዎች እየተከናወነ ይገኛልም ነው ቦርዱ ያለው።
ለተጨማሪ 15 ቀናት ተራዝሞ የነበረው ምዝገባው ከአፋር እና ሶማሌ ክልሎች ውጪ ዛሬ አርብ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር የሚጠናቀቀው፡፡
ሆኖም ምዝገባው በተራዘመበት ወቅት ተደራራቢ የበዓል ቀናት በመኖራቸው እና በህጉ መሰረት ብሔራዊ በዓላት ዝግ በመሆናቸው የመራጮች ምዝገባ ሊከናወን አለመቻለም፡፡
1 ሺ 500 መራጮች የመዘገቡ ጣቢያዎችን ለይቶ ንዑስ ጣቢያዎችን የማደራጀቱ ሂደት ጊዜ በመውሰዱም ከፍተኛ የመራጮች መጨናነቅ በምርጫ ጣቢያ ላይ ተፈጥሯል፡፡
ይህን ተከትሎ የመራጮች ካርድ በመውሰድ መምረጥ የሚችሉ ቀላል የማይባሉ ዜጎች ካርድ አለመውሰዳቸውን መገንዘቡንም ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡
ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ባደረገው ስብሰባም ምዝገባው ዛሬ ይጠናቀቅባቸው በነበሩ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ በአማራ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በሃረሪ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልል እና በሲዳማ ክልል የመራጮች ምዝገባ እስከ አርብ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለተጨማሪ 07 ቀናት እንዲከናወን ወስኗል።
በውሳኔው መሰረት መራጮች የመራጭነት ካርዳቸውን በተጠቀሱት ቀናት በአቅራቢያቸው ከሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት እንዲወስዱም ነው ቦርዱ ያሳወቀው፡፡
የቦርዱ አስፈጻሚዎች እና አስተባባሪዎች በህጉ መሰረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት እስከ ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የመራጮች ምዝገባን እንዲያከናውኑም ትዕዛዝ ሰጥቷል።