ምርጫ ቦርድ ህወሓትን "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲነት መመዝገቡን አስታወቀ
ቦርዱ ፓርቲው እንዲመለስለት ያቀረበው የህጋዊ ሰውነት ጥያቄ በተሻሻለው አዋጅም የማያሰጥ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ተመዝግቦ እንዲቀጥል ወስኛለሁ ብሏል
ህውሓት በፓርቲነት መመዝገቡ ከታወቀበት ቀን ጀምሮ ባሉት 6 ቀናት መተዳደርያ ደንቡን እንዲያጸድቅ እና አመራሮቹን እንዲያስመርጥ አዟል
የኢትየጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን "በልዩ ሁኔታ" በፓርቲነት መመዝገቡን አስታወቀ።
ቦርዱ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህውሓት) ያቀረበውንየህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ እንዳልተቀበለው ገልጿል።
ቦርዱ ቀደም ሲል ሚያዝያ 13 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ፓርቲው ላቀረበው የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ መርምሮ በዐዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት የቀድሞውን የፓርቲውን ሕልውና መመለስ የሚያስችል የሕግ ድንጋጌ የለም በማለት ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. መወሰኑን አስታውሷል፡፡
ተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ የሥነ-ምግባርን የሚመለከተው 0ዋጅ በዓመፅ ተግባር ተሠማርቶ ለተሠረዘ ፓርቲ የቀድሞውን ኅልውና መልሶ የሚሰጥ የሕግ ድንጋጌ ያልያዘ በመሆኑ ቦርዱ በድጋሚ የቀረበለትን ሕጋዊ ሰውነት ወደነበረበት እንዲመለስ የሚለውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ነው ያስታወቀው፡፡
በተሸሻለው አዋጅ ላይ አንድ የፖለቲካ ቡድን ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመፅ ተግባር ላይ የተሣተፈ እንደሆነ እና ይህንን ተግባር ማቆሙን እና ሕገ-መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን አክብሮ ለመንቀሳቀስ መስማማቱን በሚመለከተው የመንግሥት አካል ከተረጋገጠ በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፖርቲ ሊመዘገብ እንደሚችል ተደንግጓል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሰኔ 17/2016 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በጻፈው ደብዳቤ ህወሓት ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባሩን ስላቆመ "በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፖርቲ" እንዲመዘገብ ማረጋገጫ ለቦርዱ ሰጥቷል።
በመሆኑም የፍትሕ ሚኒስቴር የሰጠውን ማረጋገጫ እና ህወሓት ያቀረባቸውን ሠነዶች መሠረት በማድረግ ህወሓት በልዩ ሁኔታ እንደ ፖለቲካ ፖርቲ እንዲመዘገብ ቦርዱ መወሰኑን አስታውቋል።
ቦርዱ እንደገለጸው የሚሰጠውም የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ "በልዩ ሁኔታ" የሚል ቃል ያለበት ሆኖ እንዲዘጋጅ ተደርጓል።
በዚህም መሠረት ይህ በልዩ ሁኔታ የመመዝገብ ውሣኔን የያዘው ደብዳቤ ለፓርቲው ከደረሰው ቀን ጀምሮ ባሉት ስድስት ቀናት መተዳደሪያ ደንቡን ማጽደቅ፣ አመራሮቹን ማስመረጥ አለበት ተብሏል።
የቅድመ ጉባዔ ዝግጅት የተመለከቱ ሥራዎችን ቦርዱ መከታተል እንዲችል ፖርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ከማድረጉ 21 ቀናት በፊት የጠቅላላ ጉባዔ የሚያደርግበትን ቀን ለቦርዱ ማሳወቅ አለበት፡፡
ጠቅላላ ጉባዔው በቦርዱ ከፀደቀ በኋላ ባሉት የአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ውስጥ ፓርቲው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እያደረገ ስለመሆን አለመሆኑ በዐዋጅ ቁጥር 1332/2016 አንቀጽ 3 መሠረት ክትትል የሚያደርግ መሆኑ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርዱ ይፋ አድርጓል፡፡