ጠ/ሚ ዐቢይ እና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኙ
ጽ/ቤቱ እንደገለጸው ይህ የፌደራል እና የክልል ኃላፊዎች የሚያደርጉት ስብሰባ በመልሶ ግንባታ እና በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ያተኩራል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በአዲስ አበባ የተገኙት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ጉዳይ እየመከሩ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
በዚህ ውይይት ላይ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊዎች በተጨማሪ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል መገኘታቸውን ጽ/ቤቱ የለጠፈው የምስል መረጃ ያሳያል።
የህወሓት ሊቀመንበር እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ከተፈረመው የፕሪቶሪያው የዘላቂ ሰላም ስምምነት በኋላ ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።
ጽ/ቤቱ እንደገለጸው ይህ የፌደራል እና የክልል ኃላፊዎች የሚያደርጉት ስብሰባ በመልሶ ግንባታ እና በስምምነቱ አፈጻጸም ላይ ያተኩራል።
የፌደራል መንግስት እና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሰላም ስምምነቱ በኋላ መሻሻሎች መኖራቸውን ቢጠቅሱም አሁንም የሚቀሩ ነገሮች እንዳሉ ሲያነሱ ይደመጣሉ።
የፌደራል መንግስት የሰላም ስምምነቱን መፈረም አንደኛ አመት መሰረት አድርጎ ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል ስምምነቱን ከመፈጸም አንጻር "እግር የመጎተት አዝማሚያ" አለ የሚል ትችት መሰንዘሩ ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ አለመፍታታቸውን በቅሬታ አንስቶ ነበር።
ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረጉን በመግለጫው የጠቀሰው መንግስት የበለጠ መተማመን ለመፍጠር በማሰብ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ የመወከል መብት እያለው ሳይወከል መቅረቱን ጠቅሷል።
ይህን ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኘሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ በፌደራል መንግስት በኩል ያልተፈጸሙ የስምምነት ነጥቦች መኖራቸውን በመጥቀስ ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት የውጭ ኃይሎችን ከትግራይ ግዛት አላስወጣም፤ ተፈናቃዮችን እንዲመለሱ አላደረገም የሚል ትችት ነበር አቶ ጌታቸው ያቀረቡት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቀናት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረቡበት ወቅት በስምምነቱ መሰረት የፌደራል መንግስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በትብብር በርካታ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል።
ባንኮች በ10ቢሊዮን ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ስራ መጀመራቸው፣ በክልሉ ያሉ አየር መንገዶች ስራ መጀመራቸው፣ የ4ጂ የቴሌ ኔትወርክ አገልግሎት መጀመሩ፣ የኢንዱስትሪዎች ስራ መጀመር እና ሌሎችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስኬት ያነሷቸው ተግባራት ናቸው።
ነገርግን ይህ በቂ አለመሆኑን እና የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።