ህወሓት ሚስጥር ለጠላት አሳልፈው ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አባረረ
ህወሓት ጥቅምት 24፣2013 ዓ.ም ከፌደራል መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ከመግባቱ በፊት ለረጅም አመታት የትግራይ ክልል ገዥ ፖርቲ ነበር
ፓርቲው እስር ላይ ከነበሩት የፖርቲው አባላት ውስጥ ዶ/ር አዲሳለም ባሌማ እና ዶ/ር ኣብርሃም ተከስተ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ አድርጊያለሁ ብሏል
ህወሓት ሚስጥር ለጠላት አሳልፈው ሰጥዋል ያላቸውን ሁለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን አባረረ።
ህወሓት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ የቀድሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂምን እና የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሄርን ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከፓርቲው አባልነት ማባረሩን አስታውቋል።
ፓርቲው እነዚህ ሁለት አባላት ሚስጥር ለጠላት አሳልፎ በመስጠት በስብሰባ መገምገማቸውን እና ይህን ተከትሎም እንዲባረሩ መደረጉን ገልጿል።
- ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያሰችል የህግ አግባብ የለም አለ
- የምርጫ ቦርድ ውሳኔ "የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን" ነው ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቃወመ
ፓርቲው እስር ላይ ከነበሩት የፖርቲው አባላት ውስጥ ዶ/ር አዲሳለም ባሌማ እና ዶ/ር ኣብርሃም ተከስተ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ አድርጊያለሁ ብሏል።
በተጨማሪም ፓርቲው እንደገለጸው ዶ/ር ሰሎሞን ኪዳነ፣ አቶ ኣፅበሃ ኣረጋዊ፣ ወ/ሮ ኪሮስ ሓጎስ፣ ዶ/ር ረዳኢ በርሀን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ በሙሉ ደምጽ ወስኗል።
ህወሓት ጥቅምት 24፣2013 ዓ.ም ከፌደራል መንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ከመግባቱ በፊት ለረጅም አመታት የትግራይ ክልል ገዥ ፖርቲ ነበር።
የግጭቱን መቀስቀስ ተከትሎ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኃይል እንቅስቃሴ ተሳትፏል በሚል ምክንያት ከህጋዊ ፓርቲነት መሰረዙ ይታወሳል።
ግጭቱ ህወሓት እና የፌደራል መንግስት በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሬቶሪያ ዘላቂ ሰላም ስምምነት ካደረጉ በኋላ ህጋዊ ሰውነቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስለት ጠይቆ ነበር።
ምርጫ ቦርድ ግን የተሰረዘን ፓርቲ እንደገና እውቅና የሚሰጥበት አሰራር እንደሌለው ገልጾ ጥያቄውን በወቅቱ ውድቅ አድርጎታል።
ህወሓትም የምርጫ ቦርድን ውሳኔ "የሰላም ስምምነቱን የሚፈታተን ነው" የሚል የተቃውሞ መልስ መስጠቱ ይታወሳል።
ህወሓት በቅርቡ ህጋዊ ሰውነቱ እውቅና በሚያገኝበት ጉዳይ ከፌደራል መንግስት ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ገልጿል።