የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ ምልክት ይፋ ሆነ
የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ ከሀገራዊ ምርጫው ጋር ግንቦት 28 ይካሄዳል መባሉ የሚታወስ ነው
የህዝበ ውሳኔ መልክቶቹ እጅ ለእጅ የተያያዙና ጎጆ ቤት መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ ጋር በጋራ የሚከናወነውን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ ምልክት ይፋ አድርጓል።
ቦርዱ ይፋ ያደረገው ሁለት ምልክቶችን ሲሆን ምልክቶቹ የተያያዘ እጅን እና ጎጆ ቤትን የሚያመለክቱ ናቸው።
ምልክቶቹ ድምጽ ሰጪዎች ህዝበ ውሳኔውን መደገፍ አለመደገፋቸውን ለመለየት እንደሚያስችሉ ታስበው የተዘጋጁ ናቸው እንደ ቦርዱ ገለጻ፡፡
“እጅ ለእጅ የተያያዙ” ምልክት “የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራቦ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ” ለሚሉ ድምጽ ሰጪዎች የተዘጋጀ መሆኑን ቦርዱ አስታውቋል።
የጎጆ ቤት ምልክት ደግሞ “የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራቦ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ የዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አካል ሆነው መቀጠላቸውን እደግፋለሁ” ለሚሉ ድምጽ ሰጪዎች የተዘጋጀ ነው፡፡
በክልሉ የሚገኙት 5 ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በየምክር ቤቶቻቸው የጋራ ክልል ለመመስረት ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡
የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሔዱት መደበኛ ጉባዔ ነው በ “ደቡብ ምዕራብ ህዝቦች” ክልልነት እንዲደራጁ ከአሁን ቀደም በመንግስት የቀረበውን ምክረ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ ያጸደቁት።
ውሳኔውን የዞኖቹ እና የልዩ ወረዳው ምክር ቤቶች ለደቡብ ክልል ም/ቤት አቅርበው ም/ቤቱ ደግሞ ወደ ፌዴሬሽን ም/ቤት መምራቱ ይታወሳል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባው ጥያቄውን ተቀብሎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ወስኗል።