አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታደርግ ከግብጽ ጉቦ የተቀበሉት ሴናተር ቦብ ሜነንዴዝ መጨረሻ ምን ሆነ?
በዋሸንግተን ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆኑት ሜነንዴዝ ከግብጽ እና ኳታር ጉቦ መቀበላቸው ተረጋግጧል
እኝህ ጉምቱ ፖለቲከኛ የፊታችን ጥቅምት ወር ላይ የእድሜ ልክ እስር እንደሚተላለፍባቸው ይጠበቃል
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንድታደርግ ከግብጽ ጉቦ የተቀበሉት ሴናተር ቦብ ሜነንዴዝ መጨረሻ ምን ሆነ?
ቦብ ሜነንዴዝ ባለፉት 40 ዓመታት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ሲሆን አሁን ላይ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው፡፡
የዘር ሀረጋቸው ከኩባ የሚመዘዘው ሜነንዴዝ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው የአሜሪካ ህግ አውጪ ምክር ቤትን ከመቀላቀላቸው በፊት የኒው ጀርሲዋ ዩኒየን ሲቲን በከንቲባነት መርተዋል፡፡
እኝህ ጉምቱ ፖለቲከኛ በፈረንጆቹ 2020 ላይ የወቅቱ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ በንቃት እንዲሳተፉ አድርገዋል ተብሏል፡፡
እንደ አሜሪካ ድምጽ ዘገባ ከሆነ ፖለቲከኛው ይህን ያደረጉት ከግብጽ ባለስልጣናት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ጉቦ ከተቀበሉ በኋላ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሶስትዮሽ ውይይት በማድረግ ላይ የነበሩ ሲሆን የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ ውይይት ወደ ዋሸንግተን እንዲመጣ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡
አሜሪካዊው ፖለቲከኛ ቦብ ሜንድዝ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ ከግብጽ ጉቦ መቀበላቸው ተገለጸ
በዋሸንግተን በተደረጉት ተከታታይ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ በጫና ወደ ስምምነት እንድትመጣ ግፊት ሲደረግ እንደነበር እና ኢትዮጵያ ስምምነቱን አልፈርምም በሚል አቋሟ መጽናቷን በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መግለጫ አውጥቶም ነበር፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፖለቲከኛው ከግብጽ እና ኳታር ኩባንያዎች ጋር ጥቅም ትስስር በመፍጠር ያልተገባ ገንዘብ ተከፍሏቸዋል የተባለ ሲሆን የሀገሪቱ ፍትህ ተቋማት ባደረጉት ምርመራ ሜነንዴዝ በጉቦ መቀበል፣ በፍትህ ማዛባት እና ሌሎችም ወንጀሎች ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ፍርድ ቤት በፖለቲከኛው ላይ የእስር እና ሌሎች ቅጣት ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ ለመጪው ጥቅምት ቀጠሮ ይዟል፡፡
ሴናተር ቦብ ሜነንዴዝ ጥፋተኛ መሆናቸውን ተከትሎ የስልጣን ጊዜው እየተጠናቀቀ ካለው የምክር ቤት አባልነታቸው በነገው ዕለት በይፋ እንደሚነሱ ኒዮርክ ታየምስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ ሴናተሩ የኒው ጀርሲ ህዝብን ወክለው የአሜሪካ ምክር ቤት አባልነታቸው በይፋ የሚያበቃ ሲሆን በምትካቸውም ፊል መርፊ እስከ ቀጣዩ ጥር ወር ድረስ እንደሚተኳቸው ተገልጿል፡፡
በቀጣይ ሕዳር ከሚደረገው ምርጫ ዝርዝር ውስጥም ፓርቲያቸው ዲሞክራት ፓርቲ በቦብ ሜኔንዴዝ ምትክ ሌላ እጩ እንደሚያዘጋጅም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሴናተር ቦብ በቀጣይ ጥቅምት ወር ላይ ፍርድ ቤት ቀርበው በፈጸሟቸው ወንጀሎች ላይ የሚተላለፍባቸውን ፍርድ ይቀበላሉ የተባለ ሲሆን የእድሜ ልክ እስራት ሊተላለፍባቸው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡