አሜሪካ በኒጀር የነበራትን ወታደራዊ የጦር ሰፈር ሙሉ ለሙሉ ለቀቀች
ኒጀር በሀገሯ ያለውን የአሜሪካ እና ፈረንሳይ ወታደራዊ ማዘዣ እንዲዘጉ ውሳኔ ማሳለፏ ይታወሳል
አሜሪካ በማዘዣው የነበሩ 200 ወታደሮቿን አስወጥታለች
አሜሪካ በኒጀር የነበራትን ወታደራዊ የጦር ሰፈር ሙሉ ለሙሉ ለቀቀች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር በሀገሯ የበርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት ወታደራዊ ማዘዣ ማዕከል ነበረች።
ሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነትን ለመከላከል በሚል በኒጀር የሰፈሩት የአሜሪካ እና ፈረንሳይ ወታደሮች አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ ለቀው ወጥተዋል።
ሀገራቱ ወታደሮቻቸውን ከኒጀር ያስወጡት ስልጣን በመፈንቅለ መንግሥት የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት ውሳኔን ተከትሎ ነው።
አሜሪካ በኒጀር ወታደራዊ መንግሥት ጦሯን እንድታስወጣ ከተነገራት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ዙሮች ወታደሮቿን ስታስወጣ ቆይታለች።
አሁን ደግሞ በመጨረሻ ዙር 200 ወታደሮቿን ከኒጀር በማስወጣት የነበራትን ወታደራዊ ማዘዣ መዝጋቷን ቢቢሲ ዘግቧል።
ሌላኛዋ ጦሯን በኒጀር አስፍራ የነበረችው ፈረንሳይ ከዚህ በፊት ሙሉ በሙሉ ወታደሮቿን እና እምባሳደሯን ማስወጣቷ አይዘነጋም።
ከምዕራባዊያን ሀገራት ጋር ሆድና ጀርባ የሆነችው ኒጀር ከሩሲያ ጋር ያላት ግንኙነት እየጠበቀ መጥቷል።
በዓለም ላይ ውድ የሆነው ዩራኒየም ማዕድን ዋነኛ መገኛ የሆነችው ኒጀር ከአፍሪካ ህብረት አባልነት መታገዷ ይታወሳል።
ኒጀርን ጨምሮ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን የተቆጣጠሩት ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ከምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ወይም ኢኮዋስ አባልነት ራሳቸውን ማግለላቸው አይዘነጋም።
ሶስቱ ሀገራት ከኢኮዋስ አባልነት ራሳቸውን ያገለሉት ድርጅቱ የምዕራባዊያን ጥቅም ማስጠበቂያ ሆኗል በሚል ሲሆን አንዳቸው በራሳቸው ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመመከት የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈራርመዋል።