በሀሰን ነስረላህ አካል ላይ ምንም ቁስል እንደሌለ የህክምና ምንጮች ተናግረዋል
የሊባኖሱ መሪ ሀሰን ነስረላህ አስከሬን እስራኤል የአየር ድብደባ በፈጸመችበት ስፍራ መገኘቱ ተነግሯል።
የሀሰን ነስረላ አስከሬን በዛሬው እለት በቤሩት ደቡባዊ ክፍል የእስራኤል የአየር ድብደባ በፈጸመችበት ስፍራ ላይ መገኘቱን ሮይተርስ የደህነነት እና የህክምና ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
የደህነነት እና የህክምና ምንጮች እንደተናገሩት ከሆነ፤ የሀሰን ነስረላህ ሰውነት ላይ ምንም ቁስል እንደሌለ እና የሞቱ መንስኤ ከፍንዳዋው ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ከፍተኛ ንዝረት ሊሆን አንድሚችል አስታውቀዋል።
የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪው ሼክ ሀሰን ናስራላህ መገደላቸውን በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ቀብሩ መች እና የት ይፈጸማል የሚለውን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የእስራኤል ጦር በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ በቤሩት በፈጸመው የአየር ጥቃት የሄዝቦላን ዋና ጸኃፊ ሀሰን ነስረላህን መግደሉን ማስታወቁን ይታወሳል።
የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሀሰን ናስራላህ በመካከለኛው ምስራቅ ስመ ጥር ከሆኑ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ናስራላህ የእስራኤልን ግድያ ለማምለጥ ለአመታት ከህዝብ እይታ ተሰውረው ቆይተው በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ሲታዩ ቆይተዋል።
መሪው በተደጋጋሚ ለህዝብ በይፋ ባይታዩም ቡድኑን ለመምራት እና ተጽዕኖውን ከማሳደግ ሰንፈው አያውቁም።
በናስራለህ የመሪነት ዘመን ሄዝቦላህ ባለስቲክ ሚሳይሎችና ሮኬቶችን ታጥቆ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ስጋትን ከመደቀኑ ባሻገር ባለፉት አስርተ አመታት በቀጠናው ጠንካራ ወታደራዊ ቡድን መሆን ችሏል።
ናስራላህ መሪ ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት ከሊባኖስ ተሻግረው የሃማስ ፣ የኢራቅ እና የየመን ታጣቂ ቡድን አባላትን ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት እና የጦር መሳርያ በማስታጠቅ ስማቸው ይነሳል።
በቀጠናው ዋና ጠላት አድርገው ከፈረጇት እስራኤል ጋር ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገብተው የተለያዩ ተልእኮዎችን በማሰናዳት ቀላል የማይባል ጉዳትን አድርሰዋል።
በ1960 በሊባኖስ የተለወለዱት ናስረላህ በምስራቃዊ ቤሩት ቦርጅ ሃሞድ መንደር ነው ያደጉት። አነስተኛ የአትክልት ሱቅ የሚያስተዳድሩት አባታቸው አብዱል ካሪም ራን ካሏቸው ዘጠኝ ልጆች መካከል የመጀመርያ ልጅ ናቸው።