እስራኤል የገደለችው የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ናስራላህ ማን ናቸው?
ከ32 አመት በፊት በ32 አመታቸው የሄዝቦላህ መሪ የሆኑት ናስራላህ የእስራኤልን የግድያ ሙከራ ለማምለጥ ለአመታት ከህዝብ እይታ ተሰውረው ቆይተዋል
እስራኤል በ2024 ብቻ በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ከ10 በላይ አመራሮችን ገድላለች
የሊብኖሱ ሄዝቦላህ መሪ ሼክ ሀሰን ናስራላህ በመካከለኛው ምስራቅ ስመ ጥር ከሆኑ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ።
ናስራላህ የእስራኤልን ግድያ ለማምለጥ ለአመታት ከህዝብ እይታ ተሰውረው ቆይተው በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ሲታዩ ቆይተዋል።
መሪው በተደጋጋሚ ለህዝብ በይፋ ባይታዩም ቡድኑን ለመምራት እና ተጽዕኖውን ከማሳደግ ሰንፈው አያውቁም፡፡
በትናንትናው እለት ግን በቤሩት በተፈጸመ የአየር ጥቃት መገደላቸውን የእስራኤል ጦር በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።
በናስራለህ የመሪነት ዘመን ሄዝቦላህ ባለስቲክ ሚሳይሎችና ሮኬቶችን ታጥቆ በእስራኤል ላይ ከፍተኛ ስጋትን ከመደቀኑ ባሻገር ባለፉት አስርተ አመታት በቀጠናው ጠንካራ ወታደራዊ ቡድን መሆን ችሏል፡፡
ከኢራን መንግስት እና ሀይማኖታዊ መሪዎች ጋር የጠበቀ ወዳጅነትን የመሰረቱት መሪው ቡድኑ ጠንካራ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ተዋናይ እንዲሆን የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡
ናስራላህ መሪ ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት ከሊባኖስ ተሻግረው የሃማስ ፣ የኢራቅ እና የየመን ታጣቂ ቡድን አባላትን ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት እና የጦር መሳርያ በማስታጠቅ ስማቸው ይነሳል፡፡
በቀጠናው ዋና ጠላት አድርገው ከፈረጇት እስራኤል ጋር ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ገብተው የተለያዩ ተልእኮዎችን በማሰናዳት ቀላል የማይባል ጉዳትን አድርሰዋል፡፡
በትላንትናው እለት በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት ለ32 አመታት ሄዝቦላህን የመሩት ሀሰን ነስረላህ ማን ናቸው፡፡
በ1960 በሊባኖስ የተለወለዱት ናስረላህ በምስራቃዊ ቤሩት ቦርጅ ሃሞድ መንደር ነው ያደጉት። አነስተኛ የአትክልት ሱቅ የሚያስተዳድሩት አባታቸው አብዱል ካሪም ራን ካሏቸው ዘጠኝ ልጆች መካከል የመጀመርያ ልጅ ናቸው፡፡
በ1975 በሊባኖስ በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት የአማል ንቅናቄ በመባል የሚታወቀውን የሺአ ሚሊሻን በመቀላቀል ወደ ፖለቲካ እና ወታደራዊው አለም ከገቡ በኋላ ናጃፍ ወደ ተባለችው የኢራን ቅዱስ ከተማ በማምራት የሺአ ሙስሊም ሀይማኖታዊ ትምህርትን ተምረዋል፡፡
በ1982 እስራል ሊባኖስን በወረረችበት ወቅት አማል ከሚባለው ታጣቂ ቡድን ተገንጥሎ በመወረጣት በመሰብሰብ ኢስላክ አማል የተሰኝ ቡድንን ተቀላቀሉ።ይህ ታጣቂ አሁን ላይ ሄዝቦላህ ወደ ሚል ስያሜ የተቀየረው ነው፡፡
በዚህ ጊዜም ለትምህርት በኢራን ባቀኑበት ወቅት በመሰረቱት ወዳጅነት የኢራን አብዮታዊ ዘብ ጠንካራ ወታደራዊ ድጋፍን በመሰብሰብ ሄዝቦላ እንዲመሰረት ወሳኝ አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡
በ1985 ሄዝቦላህ አሜሪካን እና ሶቭየት ህብረትን የእስላማዊ መርሆዎች ጠላት በሚል ከመፈርጅም ባለፈ የሙስሊም መሬቶችን ተቆጣጥራ የምትገኝውን እስራኤል ለማጥፋ እስራለሁ ብሎ ተነሳ፡፡
ናስረላህ በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ በቡድኑ ውስጥ ቀስ በቀስ በተለያዩ ሀላፊነቶች ውስጥ በማለፍ ከተራ ተዋጊነት በ1992 እስከ ቡድኑ ዋና መሪነት ደርሰዋል፡፡
ከእርሳቸው በፊት የነበሩት የሄዝቦላ መሪ አባስ አል ሙሳዊ በእስራኤል የሄሊኮፕተር ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ ነበር ነስረላህ በ32 አመታቸው የቡድኑ መንበር ላይ የተቀመጡት፡፡
ወደ ስልጣን እንደመጡ የመጀመርያ እርምጃቸው የነበረው ለቀድሞው መሪ ግድያ በሰሜን እስራኤል ላይ ሮኬት በመተኮስ የአጸፋ ምላሽ መስጠት ነበር፡፡
ከዚህ ባለፈም በቱርክ የእስራኤል ኢምባሲ መኪና ላይ የተጠመደ ቦንብ በማፈንዳት እንዲሁም በአርጄንቲና ቦነስአይረስ በእስራኤል ኢምባሲ አቅራቢያ የአጥፍቶ ጠፊ በማሰማራት በጥቃቱ የእስራኤል የደህንነት አባልን ጨምሮ 29 ሰዎች እንዲገደሉ ትእዛዝ ሰጥተዋል፡፡
በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ለአመታት በደቡባዊ ሊባኖስ ሰፍረው የነበሩት የእስራኤል ወታደሮች ከስፍራው እንዲወጡ ውጥረቱን በማርገብ በኩል ነስረላህ የሰጡት አመራር ወሳኝ ነበር፡፡
በዚህ ወቅትም ከእስራኤል ጦር ጋር ሲዋጋ የነበረውን የመጀመርያ ልጃቸውን በሞት አጥተዋል፡፡
የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ መውጣቱን ተከትሎ ሄዝቦላህ የመጀመርያውን የአረብ ድል በእስራኤል ላይ መቀዳጀቱን አውጀዋል፡፡
እስከ 2006 ባለው ጊዜም የሂዝቦላ ታጣቂዎች በፈጸሙት ድንበር ተሸጋሪ የሮኬት እና የሚሳይል ጥቃት ከስምንት በላይ የእስራኤል ወታደሮች ተገድለዋል፡፡
ይህን ተደጋጋሚ ጥቃት ተከትሎ ዳግም ውጥረት ሲነግስ እስራኤል በደቡባዊ ቤሩት የቡድኑ ጠንካራ ይዞታ ላይ ከፍተኛ የአየር ድብደባ ስታደርስ የነስረላህ መኖርያ ቤቶች እና ቢሮዎች ኢላማዎች ነበሩ። ሄዝቦላ በበኩሉ ከ4 ሺህ በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሷል፡፡
በ2009 አዲስ የፖለቲካ ማኒፌስቶ በማዘጋጀት ከእስራኤል እና አሜሪካ ጋር ያለውን ጠላትነት በማጠናከር በመካከለኛው ምስራቅ የሁለቱን ሀገራት ተጽዕኖ ለመከላከል በሙሉ አቅሙ እንደሚታገል አስታወቆ ነበር፡፡
በሶርያው ጦርነትም የሄዝቦላህ ወታደሮችን በመላክ ከኢራን ጎን ተሰልፈው የበሽር አላሳድ መንግስትን በመደገፍ ተዋግተዋል፡፡
በነዚህ ሂደት ውስጥ ከምእራባውያን እና ከእስራኤል ጋር ካላቸው ጥል ከኢራን ጋር ባለቸው ወዳጅነትም በአካባቢው ከፍተኛ ስጋትን ደቅነው ቆይተዋል፡፡
የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ ደግሞ ከእስራኤል ጋር ዳግም ወደ ውጥረት ውስጥ የገባው ቡድኑ ከጥቅምት 7፣ 2023 ጀምሮ ወደ እስራኤል ከ8 ሺህ በላይ ሮኬት እና ሚሳኤሎች አስወንጭፏል፡፡
የቡድኑ መሪ ሀሰን ናስረላህም በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ የሚገኝው በደል እስካልቆመ እና እስራኤልም ጦሯን ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ ካላስወጣች የሮኬት ጥቃት ማድረሳቸውን እንደሚቀጥሉ በይፋ በተደጋጋሚ አስታውቀዋል፡፡
ህይወታቸውን ያሳጣቸውም ይሄው ሃማስን ደግፈው በአዲስ መልክ ከቴልአቪቭ ጋር የገቡበት ውጥረት እንደሆነ ይነገራል፡፡
እስራል የጋዘው ጦርነት ከተቀሰቀሰ አንስቶ በሂዝቦላ የተለያ ይዞታዎች ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች በተለያየ የሀላፊነት እርከን ላይ የነበሩ ከአስር በላይ የቡድኑ አመራሮችን ገድላለች፡፡
ለሶስት አስርተ አመታት ከእስራኤል ስል ኢላማዎች አምልጠው የነበሩት ሀሰን ናስረላህ በትላንትናው እለት በተቀነባበረ ጥቃት በምድር ውስጥ በሚገኝ ቢሯቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ህይወታቸው አልፏል፡፡