“በቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ የደረሰው አደጋ በኩባንያው እና ባለስልጣኑ ጥፋት ያጋጠመ ነው”-የአሜሪካ ኮንግረስ
ኮንግረሱ 18 ወራት የወሰደውን የምርመራ ውጤቱን ይፋ አድርጓል
ቦይንግ ከኤርባስ ጋር ለመፎካከር ሲል ከጥራትና ደህንነት ይልቅ ለዋጋ ቅድሚያ ሰጥቷል
ኮንግረሱ የቦይንግ አውሮፕላኖች አደጋ በካምፓኒውና በአቪዬሽን ባለስልጣኑ ጥፋት ያጋጠሙ ናቸው አለ
በኢትዮጵያና በኢንዶኔዥያ የመንገደኞች አውሮፕላኖች ላይ የደረሰው አደጋ በአውሮፕላኖቹ አምራች ኩባንያ ቦይንግ እና በአቪዬሽን አስተዳደር ባለስልጣኑ ጥፋት ያጋጠሙ መሆናቸውን የአሜሪካ ኮንግረስ አስታወቀ፡፡
አደጋዎቹ በምህንድስና እንከኖች፣ በደካማ አመራርና ክትትል ማነስ ያጋጠሙ ናቸው ያለው ኮንግረሱ በአደጋዎቹ ምክንያት የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በመላው ዓለም ከበረራ ውጭ እንዲሆኑ መደረጉን ገልጿል፡፡
ላለፉት 18 ወራት የአደጋዎቹን መንስዔዎች ሲመረምር የነበረው የኮንግረሱ የትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ኮሚቴ የምርመራ ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በውጤቱ መሰረትም ተቀዳሚ ምክንያቶች ናቸው የተባሉና ከአውሮፕላኖቹ ዲዛይን፣ፍብረካ እና ማረጋገጫ የመስጠት ሂደቶች ጋር የተያያዙ ችግሮች ቀርበዋል፡፡
ቦይንግ ከፈረንሳዩ አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኤርባስ አዳዲስ ምርቶች ጋር ለመፎካከር ሲል ከጥራትና ደህንነት ይልቅ ባነሰ ዋጋ ለማምረት ቅድሚያ ሰጥቷል የሚል ወቀሳ በዴሞክራት የኮሚቴው አባላት ቀርቧል፡፡
ጥቂት የማይባሉ አውሮፕላኖችን ቁልቁል ላልዘገዘጉ የበረራ ቁጥጥር መተግበሪያዎችም (MCAS) ተገቢውን ትኩረት አልሰጠም ያሉት አባላቱ ከአቪዬሽን ባለስልጣኑ የሚሰጡ መረጃዎችን እንደሚደብቅ እና ልል የቁጥጥርና ክትትል ተግባራት እንደነበሩም ነው የተናገሩት፡፡
ባለስልጣኑ እና ባለሙያዎቹ ለኩባንያው ያሳዩትን ያልተገባ ወገኝተኝነትም ኮንነዋል፡፡
ሁለቱም አካላት ለደህንነት ጉዳዮች እና ግልጸኝነት ቀዳሚ ትኩረትን በመስጠት ችግሮቹን እንዲያስተካክሉም አዘዋል፡፡
በሁለቱ አደጋዎች 346 ሰዎች ማለቃቸው የሚታወስ ነው፡፡