ይህን ያደረገው አውሮፕላኖቹ በምርት ወቅት በገጠማቸው ችግር ምክንያ ነው
በ787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖቹ ዋና ክፍል እክል እንደገጠመው ቦይንግ አስታወቀ
በአንዳንድ አየር መንገዶች 787 ድሪምላይነር አውሮፕላኖችን ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ ማድረጉን አሜሪካዊው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ አስታወቀ፡፡
አውሮፕላኖቹ ከአገልግሎት ውጭ እንዲሆኑ የተደረጉት በምርት ወቅት በዋና አካል ክፍላቸው (fuselage) ያጋጠሙ ሁለት ችግሮች እንዳሉ በመረጋገጡ ነው ያለው ኩባንያው እስካሁን 8 አውሮፕላኖች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
የችግሮቹን ምንጭ ለማወቅ ጥረት እያደረግሁ ነው ያለም ሲሆን ለአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር ስለጉዳዩ ማስታወቁንም ገልጿል፡፡
“ችግር እንዳለባቸው የተለዩትን 8 አውሮፕላኖች የሚገለገሉ አየር መንገዶችን ወዲያውኑ ነው ስለሁኔታው ያሳወቅናቸው፤ አውሮፕላኖቹ እስከሚጠገኑ ድረስ በጊዜያዊነት ግልጋሎት ላይ እንዳይውሉም አድርገናል” ሲሉም ነው የኩባንያው ቃል አቀባይ ፒተር ፔድራዛ ለሮይተርስ የተናገሩት፡፡
አየር መንገዶቹ ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ሲንጋፑር ኤርላይንስ እና ኤር ካናዳ ናቸው፡፡
የቴክኒክ ችግር ነበረባቸው በተባሉ የቦይንግ አውሮፕላኖች ምክንያት ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ እና በኢንዶኔዥያ በደረሱ እጅግ አስከፊ አደጋዎች የበርካቶች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው፡፡