ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በጦርነት ከምትታመሰው ዩክሬን እንዴት ሾልከው ወደ አሜሪካ ሊሄዱ ቻሉ?
ዘሌንስኪን ከዩክሬን የማስወጣት ሂደት የተከናወነው በሚስጥር መሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ
የአሜሪካ ባለስልጣናት የፕሬዝዳንት ዘሌንሰኪን ጉብኝት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ በዛሬው እለት ወደ አሜሪካ ማቅናታቸው እየተነገረ ነው፡፡
“ለመሆኑ ዘሌንሰኪ ላለፉት 10 ወራት በጦርነት እየታመሰች ከቆየችው ዬክሬን ወደ አሜሪካ እንዴት ሾልከው ሊወጡ ቻሉ ?” የሚለው ግን በርካቶች የሚያነሱት ጥያቄ ሆኗል፡፡
አል ዐይን ኒውስ ጉዳዩን በተመለከተ በፍርስራሽ ከተሞላችው ዩክሬን እስከ ዋይት ሃውስ የነበረውን ሂደት ለማጣራት ያደረገውን ሙከራ እንደሚያመለክተው ከሆነ ፤ፕሬዝዳንቱን የማስወጣት ሂደት የተከናወነው ሚስጥዊ በሆነና ከፍተኛ ጥንቃቄ በተሞላበት አኳሃን ነው፡፡
በዚህም መሰረት ፕሬዝዳንቱ ከኪቭ እንዲወጡ የተደረገበት ሂደት በትዊተር ገጻቸው ወደ አሜሪካ እየተጓዙ መሆናቸው እስከገለጹባት አጋጣሚ ዘሌንስኪ ከየዩክንን ምድር ለቀው ወደ ዋሽንግተን ስለማቅናታቸው የታወቀ ነገር አልነበርም፡፡
“የዩክሬንን ጽናት እና የመከላከል አቅም ለማጠናከር ወደ አሜሪካ እየሄድኩ ነው ።በኮንግሬስ ንግግር ካደረኩ በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው ትብብር እወያያለሁ ። የሁለትዮሽ ስብሰባዎችም ይኖራሉ" ሲሉም ነበር ፕሬዝዳንቱ በትዊትር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ የገለጹት፡፡
ፕሬዝዳንቱ ይህን ይበሉ እንጅ የዘሌንሰኪ መምጣትን በተለመከተ የተጠየቁት የአሜሪካ የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ “እስካሁን አናውቅም፡፡ አናውቅም” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሌሎች የአሜሪካ ባለስልጣናትም በተመሳሳይ ከጉብኝቱ በፊት ስላለው የጸጥታ ዝግጅት ምንም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በትናንትናው እለት ማክሰኞ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን ከጋዜጠኞች ጋር በስልክ ባደረጉት ኮንፈረንስ ይህ በግልጽ ታይቷል።
በዚህም “ ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ወደ ዋሽንግተን የተጓዙት በአሜሪካ አውሮፕላን ነው ወይስ አይደለም? ” የሚለውን ጉዳይ ማወቅ አልተቻለም፡፡
ባለስልጣኑ ጆ-ባይደን እና ዜለንስኪ በታህሳስ 11 ቀን በስልክ ተገናኝተው ስለጉብኝቱ አውርተው እንደነበር ግን አልሸሸጉም፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዘሌንስኪ ወደ አሜሪካ ያቀኑት ፕሬዝዳንት ባይደን ባቀረቡላቸው ግብዣ እንደሆነም አክለዋል ባለስልጣኑ፡፡
ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት ረዳቶች ጋር እንደሚወያዩና በሀገሪቱ ኮንግረስን ንግግር እንደሚያሰሙም ሮይተርስ ዲፕሎማቲክ ምንጮቹን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል፡፡
የዩክሬኑ መሪ ባህር ማዶ ተሻግረው የሚያደርጉት ጉብኝት የካቲት 24 ከተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ወዲህ የሚደረግ የመጀመሪያውና ታሪካዊ ጉብኝት መሆኑ ነው፡፡
ጉብኝቱ ላላፉት 10 ወራት በበይነ መረብ ብቻ ሲያወሩ የነበሩት ሁለቱም መሪዎች በአካል ተገናኝተው በተለያዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ የሚመክሩበትም ነው፡፡