ከአሜሪካ የአቪዬሽን አስተዳዳር እና ከሌሎችም ተቆጣጣሪ ተቋማት የአገልግሎት ፍቃድ ገና ሳያገኝ ነው ምርት የጀመረው
ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖችን ማምረት ጀመረ
አሜሪካዊው አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖችን በአነስተኛ ቁጥር ማምረት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ምርቱ ዋሽንግተን ሬንተን በሚገኘው የኩባንያው ፋብሪካ ነው የተጀመረው፡፡
ጥራትና ጥንካሬ ኖሮት እንዲመረት ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም ነው የኩባንያው ፕሬዝዳንት እና የ737 ፕሮግራሞች ማናጀር ዋልት ኦዲሾ ለኤ.ኤፍ.ፒ የተናገሩት፡፡
ሆኖም ኩባንያው ከአሜሪካ የአቪዬሽን አስተዳዳር እና ከሌሎችም ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች የአገልግሎት ፍቃድ ገና አላገኘም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም ነው ምርት የጀመረው፡፡
የአደጋዎቹ ተጎጂ ቤተሰቦች እና የአየር መንገዶቹ የካሳ ክፍያ ሁኔታም ገና የመጨረሻ እልባት አላገኘም፡፡ በህግ ሂደትም ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በኢንዶኔዥያው ላየን ኤይር ከደረሱት ተከታታይ አደጋዎች በኋላ ማክስ 737ን ማምረት አቁሞ ነበረ፡፡
በተለይ ከኢት-302 አደጋ በኋላ የማክስ 737 የበረራ አገልግሎቶች ሁሉ ተቋርጠው ነበረ፡፡
ለባለፉት 12 ወራትም አውሮፕላኑ አሉበት ከተባሉ የቴክኒክ ችግሮች ጋር በተያያዘ በየትኛውም ሃገር አልበረረም፡፡