75 ነፍሰጡር ህንዳውያን ዛሬ ምሽት ከዱባይ ወደ ሃገራቸው ይመለሳሉ ተብሏል
ህንድ በተለያዩ ሃገራት የሚገኙ ዜጎቿን ልትመልስ ነው
በዱባይ ይኖሩ የነበሩ 75 ነፍሰጡር ህንዳውያን ወደ ሃገራቸው ሊመለሱ ነው ተብሏል፡፡ በደቡብ ምዕራባዊ ህንድ ወደምትገኘው ኮቺ ከተማ ዛሬ እንደሚበሩም ነው የተነገረው፡፡
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የሚኖሩ እና ሚሰሩ እንዲሁም ለጉብኝት በሚል ወደ ዱባይ አቅንተው የነበሩ ህንዳውያንን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመጠበቅ ወደ ሃገራቸው የመመለሱ ተግባር ሁለተኛ ዙር በረራ ዛሬም ቀጥሎ ያመሻል፡፡
75ቱ ነፍጡሮች ከሌሎች ተጓዦች እና የበረራ አባላት ጋር በመሆን በጤና ባለሙያዎች እንክብካቤ እየተደረገላቸው ዛሬ ምሽት በ’ኢለቭን ኤይር ኢንዲያ ኤክስፕረስ‘አየር መንገድ ወደ ኮቺ ይበራሉ፡፡
ተጓዦቹ ኮቺ ሲደርሱ አስፈላጊው ሁሉ የቫይረሱ ምርመራ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡
ከዱባይ የሚደረጉ እያንዳንዱ በረራዎች ከ200 እስከ 250 ህንዳውያንን ያሳፍራሉ፡፡
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የተሰማራው የህንድ ተልዕኮ ብቻ ከ197 ሺ ዜጎች የ‘መልሱን’ ጥያቄ እንደቀረበለት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ህንድ ከግንቦት 16 ጀምሮ በ32 የዓለም ሃገራት የሚገኙ 200 ሺ ገደማ ዜጎቿን እንደምትመልስ አስታውቃለች፡፡
‘ቫንዴ ብሃራት’ (Vande Bharat Mission) በተሰኘው በዚህ ህንዳዉያኑን ከተለያዩ ሃገራት የማጓጓዝ ተልዕኮ እስካሁን 2 ሺ 79 ሰዎችን በአስራ አንድ በረራዎች ለማጓጓዝ ተችሏል፡፡
ከተጓዦቹ ውስጥ 190ው ነፍሰጡሮች፣ 760ው በዩ.ኤ.ኢ በተለያዩ ስራዎች ላይ የነበሩ፣ 438ቱ ለመመለስ ተቸግረው የነበሩ ቱሪስቶችና ተማሪዎች ቀሪዎቹ ደግሞ ሌሎች ናቸው፡፡
ተልዕኮው በሁለት የተለያዩ ዙሮች የሚፈጸም ነው፡፡ ዛሬ በሚጀመረውና እስከ መጪው ረቡዕ በሚዘልቀው መጀመሪያው ዙር የተልዕኮው ክፍል 15 ሺ ገደማ ህንዳውያን ከ12 ሃገራት በ64 በረራዎች ይጓጓዛሉ፡፡
በበረራ ቡድን አባላት (ክሩው) የኮሮና ቫይረስ ምርመራ በመዘግየቱ ምክንያት የተራዘመው ዜጎችን አሜሪካና እንግሊዝን ከመሳሰሉ ሃገራት የማውጣቱ በረራ በመጪው ሃሙስ ይጀመራል፡፡ ተጓዦቹ በራሳቸው ወጪ ነው ወደ ሃገራቸው የሚመለሱት፡፡
የማጓጓዙ ስራ በዋናነት በሃገሪቱ አየር መንገድ ‘ኤር ኢንዲያ’ ይፈጸማል ተብሏል፡፡ ተልዕኮው በሃገሪቱ የጦር መርከቦች ጭምር የሚፈጸም ነው፡፡
ህንድ ከአሁን ቀደም የባህረ ሰላጤው ቀውስ በተጋጋለበት ጦርነት ወቅት 170 ሺ ዜጎቿን ከኩዌት አስወጥታለች፡፡