የቦይንግን የጥራት ችግር ያጋለጠው ሁለተኛው ሰው በድንገት ህይወቱ አለፈ
የቦይንግ ኩባንያ ችግሮችን ያጋለጠው የመጀመሪያው ሰራተኛ ከሁለት ወር በፊት ህይወቱ ማለፉ ይታወሳል
ሁለቱ የቀድሞ ሰራተኞች ቦይንግ ኩባንያ የ737 ማክስ አውሮፕላኖች የጥራት ችግሮችን ችላ ብሏል ብለው ነበር
የቦይንግን የጥራት ችግር ያጋለጠው ሁለተኛው ሰው በድንገት ህይወቱ አለፈ፡፡
የዓለማችን ቁጥር አንድ አቪዬሽን ኩባንያ የሆነው የአሜሪካው ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ ችግሮች ማጋጠማቸውን ተከትሎ ደንበኞቹን እና የገንዘብ ኪሳራዎችን በማስተናገድ ላይ ነው፡፡
ንብረትነታቸው የአላስካ እና ዩናይትድ አየር መንገዶች የሆኑ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖች በበረራ ላይ እያሉ መስኮት እና በራቸው መገንጠሉን ተከትሎ በቦይንግ ኩባንያ ምርቶች ላይ የጥራት ችግሮች እንዳሉ በስፋት ተሰራጭተዋል፡፡
የድርጅቱ ሰራተኞች ስለ አውሮፕላን ምርቶቹ የጥራት ጉድለት ለተለያዩ ሚዲያዎች የተናገሩ ሲሆን ሚስጥሮቹን ካወጡ ሰራተኞች መካከል ጆን ባርኔት ከሁለት ወር በፊት በመኖሪያ ቤቱ ሞቶ መገኘቱ ይታወሳል፡፡
አሁን ደግሞ ቦይንግ ኩባንያ የምርቶቹን ጥራት ጉድለት ችላ ይል እንደነበር ለሚዲያዎች የተናገረው ጆሽዋ ዲን የተሰኘው ሰራተኛ በድንገት ህይወቱ እንዳለፈ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ዲን በመልካ ጤንነት ላይ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ድንገተኛ ኢንፌክሽን አጋጥሞት ህይወቱ አልፏል ተብሏል፡፡
የቦይንግ ኩባንያ ሚስጢሮችን ያጋለጠው ሰው ሞቶ ተገኘ
ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ከሚሰራው ስፕሪት ኤሮስፔስ በተሰኘው ድርጅት ተቀጥሮ ሰራ የነበረው ዲን ሚስጡር በማውጣቱ ምክንያት ከስራ እንደተባረረ ከዚህ በፊት በነበረው ቃለመጠይቆች ላይ ተናግሮ ነበር፡፡
የሟች ጠበቃ ብሪያን ኖውልስ እንዳሉት ከሆነ ዲን የተሰማውን እና ያመነበትን ከመናገር ወደኋላ የማይል ጠንካራ ሰው እንደነበረ ሞቱም ለአቪዬሽን ቤተሰቦች ትልቅ ጉዳት ነው ብሏል፡፡
የ45 ዓመቱ ዲን ከዚህ በፊት የስትሮክ እና ከአተነፋፈስ ጋር የተያያዙ ህመሞች እንዳሉበት ወላጅ እናቱ ተናግረው እንደነበርም ተገልጿል፡፡
የዲንን መሞት ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ሲያትል ታየምስ የተሰኘው ሚዲያ ዲን በጥሩ ጤንነት ላይ እንደነበር እና ጤናማ ህይወቱን እየመራ ነበር ብሏል፡፡