ግለሰቡ በቦይንግ ኩባንያ ላይ የጥራት ችግሮች እና ምቹ የስራ አካባቢ እንደሌለ መናገሩ ይታወሳል
የቦይንግ ኩባንያ ሚስጢሮችን ያጋለጠው ሰው ሞቶ ተገኘ፡፡
ጆን ባርኔት የተሰኘው አሜሪካዊ በግዙፉ ዓለማችን የአቪዬሽን ተቋም ቦይንግ ኩባንያ ውስጥ ለ32 ዓመታት ሰርቷል፡፡
ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ ቦይንግን የለቀቀው ይህ የቀድሞ ሰራተኛ በድርጅቱ ውስጥ በጥራት ተቆጣጣሪነት የሰራ ሲሆን ስለ ድርጅቱ በርካታ ሚስጢሮችን ይፋ አድርጓል፡፡
በተለይም ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ በ737 ማክስ 9 አውሮፕላን ምርቶች ላይ የጥራት ችግር ከተከሰቱ በኋላ ይህ ሰራተኛ በቦይንግ ምርቶች የጥራት ጉድለቶች እንዳሉ ለበርካታ ብዙሃን መገናኛዎች ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡
ይህ ግለሰብም በደቡባዊ ካሮላይና በመኖሪያ ቤቱ ሞቶ እንደተገኘ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ እንደዘገባው ከሆነ ባርኔት በሽጉጥ ራሱን አጥፈቷል፡፡
ይሁንና የባርኔት ጠበቃ ደንበኛው ራሱን አጥፍቷል ብሎ እንደማያምን ለዚሁ ሚዲያ ተናግሯል፡፡
ጠበቃው አክሎም " ባርኔት በጥሩ ስነ ልቦና ላይ ነበር፣ ስለ ወደፊቱም የነበረው እቅድ ጥሩ የሚባል ነበር ራሱን አጥፈቷል የሚል እምነት የለኝም " ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ለመግዛት የተስማማችው ቦይንግ 777X -9 አውሮፕላን የተለየ ነገር ይዟል?
የቀድሞ ቀጣሪ ድርጅቱ ቦይንግ በበኩሉ በባርኔት ሞት ማዘኑን ገልጾ ከቤተሰባቸው እና ጓደኛቸው ጎን እንደሚቆም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ ካሳለፍነው ጥር ወር ጀምሮ በተፈጠሩ የ737 ማክስ 9 አውሮፕላን ጥራት ችግሮች ጋር በተያያዘ የምርት መዘግየት፣ አክስዮን ዋጋ መቀነስ እና የምርት መስተጓጎል ችግሮች አተከስተዋል፡፡
የአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣንም ቦይንግ ኩባንያ 737 ማክስ 9 አውሮፕላንን እንዳያመርት፣ የተስተዋለበትንም የጥራት ችግር በሶት ወራት ውስጥ እንዲፈታ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
ቦይንግ በበኩሉ የ737 ማክስ 9 አውሮፕላን ምርት ሀላፊን ከሀላፊነት ያነሳ ሲሆን በ90 ቀናት ውስጥ የተከሰቱ የጥራት ችግሮችን እንደሚፈታ አስታውቋል፡፡