ቦይንግ ከኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ 200 ሚሊየን ዶላር ተቀጣ
በቦይንግ ኩባንያ ላይ የገንዘብ ቅጣቱን የጣለው የአሜሪካ የደህንነት ኮሚሽን ነው
ኩባንያው ቅጣት የተጣለበት የማክስ 737 አውሮፕላን የደህንነት መረጃን በመደበቁ ነው ተብሏል
ቦይንግ ከኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ 200 ሚሊየን ዶላር ተቀጣ።
በፈረንጆቹ 2018 እና 2019 ላይ የአሜሪካው ግዙፍ የአቪዬሽን ተቋም ቦይንግ ኩባንያ ምርት የሆኑ ሁለት አውሮፕላኖች ተከስክሰው የ346 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል።
- ቦይንግ በኢትዮጵያው አውሮፕላን አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦች ካሳ ለመክፈል ተስማማ
- “በቦይንግ አውሮፕላኖች ላይ የደረሰው አደጋ በኩባንያው እና ባለስልጣኑ ጥፋት ያጋጠመ ነው”-የአሜሪካ ኮንግረስ
ማክስ 737 የተሰኘ ስያሜ ያላቸው እነዚህ አውሮፕላኖቹ ንብረትነታቸው የኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች ነበሩ።
የአውሮፕላኖቹ አምራች የሆነው ቦይንግ ኩባንያ ምርቱ የደህንነት ችግር እንዳለበት መረጃ ቢኖረውም መረጃውን ይፋ አለማድረጉን የአሜሪካ የደህንነት እና ልውውጥ ኮሚሽን ባደረገው ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል።
በዚህም መሰረት ቦይንግ ኩባንያ መረጃውን ለህዝብ ይፋ ባለማድረጉ እና ለጉዳቱ ዋነኛ ጥፋተኛ በመሆኑ በኮሚሽኑ እንደሚቀጣ ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ቦይንግ ኩባንያ የ200 ሚሊየን ዶላር ቅጣት የተጣለበት ሲሆን የቅጣት ገንዘቡ ለተጎጂዎች እንደሚከፈልም ተገልጿል።
ቦይንግ ኩባንያ ንብረትነቱ የኢንዶኔዥያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመከስከሰ በኋላ በሰጠው መግለጫ ማክስ 737 አውሮፕላን ከሌሎች የቦይንግ ምርት ከሆኑ አውሮፕላኖች ሁሉ የተሻለ ደህንነት አለው ማለቱ ይታወሳል።
ኩባንያው ይሄንን መረጃውን ይፋ ባደረገ ጥቂት ወራት ውስጥ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ማክስ 737 አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ወደ ኬንያ ናይሮቢ እየበረረ እያለ ተከስክሷል።
ይህ አውሮፕላን ያላቸው የዓለማችን አየር መንገዶች ከሁለቱ አደጋዎች በኋላ ከበረራ ያገዱ ቢሆንም አሁን ላይ ደህንነቱ ተሻሽሏል በሚል ወደ በረራ መልሰውታል።