ቦይንግ ኩባንያ ያለበትን የደህንነት ችግር በሶስት ወራት ውስጥ እንዲፈታ ተጠየቀ
የአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣን ቦይንግ ኩባንያ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖችን እንዳያመርት ማገዱ ይታወሳል
ቦይንግ ኩባንያ በበኩሉ የባለስልጣኑን ማስጠንቀቂያ እንደሚቀበል አስታውቋል
ቦይንግ ኩባንያ ያለበትን የደህንነት ችግር በሶስት ወራት ውስጥ እንዲፈታ ተጠየቀ፡፡
የዓለማችን ግዙፉ የአቪዬሽን ኩባንያ የሆነው ቦይንግ ከሁለት ወር በፊት 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በበረራ ላይ እያለ መስኮቱ መገንጠሉን ተከትሎ አውሮፕላኖቹ ከበረራ እንዲታገዱ ተደርጎ ነበር፡፡
ንብረትነቱ የዩናይትድ አየር መንገድ የሆነው ይህ አውሮፕላን መንገደኞችን አሳፍሮ በመብረር ላይ እያለ ያጋጠመው ክስተት በኩባንያው ምርቶች ላይ የደህንነት ችግሮች እንዳሉ አመላክቷል፡፡
በዚህ ምክንያትም ቦይንግ ስሪት የሆኑ 737 ማክስ 9 አውሮፕላኖችን የገዙ አየር መንገዶች ከበረራ ያወረዱ ሲሆን የአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣንም ቦይንግ ይህ አውሮፕላንን እንዳያመርት አግዷል፡፡
ባለስልጣኑ አሁን ባወጣው መግለጫ ቦይንግ ኩባንያ በአውሮፕላኑ ላይ ያለበትን የጥራት ችግር በ90 ቀናት ውስጥ እንዲፈታ አሳስቧል፡፡
የቦይንግ ኩባንያ ስራ አስኪጅ ዴቭ ካልሁን በአቪዬሽን ባለስልጣን የተሰጣቸው ጊዜ በቂ መሆኑን ተናግረው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ችግሩን እንፈታለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ቦይንግ አምባሳደር ሔኖክ ተፈራን የአፍሪካ ዳይሬክተር አድርጎ ሾመ
ስራ አስኪያጁ አክለውም በአውሮፕላኑ ላይ ያለውን ችግር ለይተናል፣ ችግራችንን ለማስተካከል ዝግጁ ነን ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት ቦይንግ ሰራሽ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዢያ ተከስክሰው 346 መንገደኞች መሞታቸው ይታወሳል፡፡
ይህን ተከትሎም ቦይንግ በምርቶቹ ላይ ያለበትን የደህንነት ችግሮች እንደሚፈታ ከአሜሪካ አቪዬሽን ባለስልጣን ጋር ውል የገባ ሲሆን ከሁለት ወር በፊት የተከሰተው ክስተት ይህን ውል ስለመጣሱ በሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስቴር ምርመራ እየተካሄደበት ይገኛል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ ከአንድ ወር በፊት የ737 ማክስ አውሮፕላን ምርት ሃለፊን ከምርት ጥራት እና ቁጥጥር ጋር በተያያዘ ሃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል ከሀላፊነት ማንሳቱ ይታወሳል፡፡