ኢትዮጵያ ለመግዛት የተስማማችው ቦይንግ 777X -9 አውሮፕላን የተለየ ነገር ይዟል?
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፉን ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖች ለመግዛት ስምምነት ተፈራርሟል
ግዙፉ 777X -9 አውሮፕላን የነዳጅ ወጪን እስከ 10 በመቶ የሚቀንስ ነው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግዙፉን ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖችን ከቦይንግ ኩባንያ ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።
አየር መንገዱ የቦይንግ አዲስ ምርት የሆኑትን በቅርብ ግዜ እና በሂደት የሚረከባቸውን የ20 ቦይንግ 777X-9 አውሮፕላኖችን ለማስገባት የሚያስችለውን ስምምነት ባሳለፍነው ማክሰኞ ከቦይንግ ጋር ተፈራርሟል።
በስምምነቱ መሰረት አየር መንገዱ ለመግዛት የፈረመባቸው 8 አውሮፕላኖችን የሚረከበው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ2027 ጀምሮ እስከ 2030 ድረስ መሆኑም የተጠቁሟል።
በዚህም 3ቱ በ2027 3ቱ በ2029 እንዲሁም 2ቱ በ 2030 የሚረከቡ መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ 777X (777-9) አውሮፕላኖች ግዢ በመፈጸም ከአፍሪካ ቀዳሚ ያደርገዋል።
ቦይንግ 777X -9 አውሮፕላን የተለየ ነገር ይዟል?
ቦይንግ 777X በዓለም ግዙፉ ባለሁለት ሞተር ጄት አውሮፕላ ሲሆን፤ በሁሉም የአፈጻጸም ዘርፍ ተወዳዳሪ የለውም ተብሎለታል።
አውሮፕላኑ በኤሮዳይናሚክስ እና በሞተሮች አዳዲስ ፈጠራዎች፣ የነዳጅ ፍጆታና ወጪን 10 በመቶ እንዲሁም የስራ ማስኬጃ ወጪዎችን በ10 በመቶ ዝቅ እንደሚያደርግም ተነግሯል።
ቦይንግ 777X -9 በአንድ ጊዜ በርካታ መንገደኞችን ማሳፈር የሚችል ሲሆን፤ ይህም አውሮፕላኑ 50 የቢዝነስ እና 390 የኢኮኖሚ በአጠቃላይ 440 መቀመጫዎች አሉት።
አውሮፕላኑ በአንድ በረራ ወቅት የሚሸፍነው ርቀትም 13 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር እንደሆነም የቦይንግ ኩባያ መረጃ ያመለክታል።
አውሮፕላኑ 70.86 ትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ የክንፉ ስፋትም በሚዘረጋበት ጊዜ 71.75 ሜትር፤ በምድር ላይ ደግሞ 64.85 ሜትር ነው ተብሏል።
ቦይንግ 777X አውሮፕላን ሁለት GE9X, ሞተር የተገጠመለት ሲሆን፤ ሞተሩም GE አቪዬሽን የተመረተ ነው።
አውሮፕላኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በረራ ያደረገው በፈረንጆች አቆጣጠር 2020 መሆኑን የተነገረ ሲሆን፤ 65 ቶን የመሸከም አቅም እንዳለውም ተመላክቷል።