ቦይንግ 17 ሺህ ሰራተኞቹን ሊያሰናብት ነው
የአሜሪካው ኩባንያ የሰራተኞች አመጽ እና ከምርት ጥራት ጋር በተያያዘ የሚቀርቡበት ወቀሳዎች ፈተና ውስጥ ጥለውታል
ቦይንግ የ777ኤክስ አውሮፕላኖችን የሚያስረክብበትን ቀን ማሸጋገሩን አስታውቋል
ግዙፉ የአሜሪካ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ 17 ሺህ ሰራተኞቹን ሊቀንስ ነው።
ኩባንያው የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ በቀጠለበትና ከጥራት ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች በበዙበት ወቅት ነው 10 በመቶውን የሰው ሃይሉን ለመቀነስ የወሰነው።
የቦይንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኬሊ ኦርትበርግ ለሰራተኞች በላኩት የኢሜል መልዕክት “የስራ አስኪያጆችም ሆነ መደበኛ ሰራተኞች” ስራ አደጋ ላይ መውደቁን አመላክተዋል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
ቦይንግ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ክንፉ ኪሳራ ሊገጥመው እንደሚችልና የ777ኤክስ አውሮፕላኖች ማስረከቢያ ቀን እንደሚገፋም ነው የገለጸው።
ከ33 ሺህ በላይ ሰራተኞቹ በስራ ማቆም አድማ ላይ የሚገኙበት ቦይንግ በቀጣይ ወራት 17 ሺህ ሰራተኞችን ለመቀነስ የወሰነው “ኩባንያው ካለበት አሳሳቢ ሁኔታ በፍጥነት እንዲያገግም ነው” ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው ኬሊ ኦርትበርግ።
ቦይንግ ከ13 አየርመንገዶች እስከ መስከረም 2024 ድረስ 503 የ777ኤክስ አውሮፕላን ትዕዛዝ ደርሶታል።
ይሁን እንጂ የሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ የበረራ ሙከራዎች ማድረግ ስለማይቻል አውሮፕላኑን በተያዘለት ጊዜ ማቅረብ እንደማይችል ገልጿል።
ዋና ስራ አስፈጻሚውም “ለደንበኞቻችን የመጀመሪያውን 777ኤክስ አውሮፕላን ከ2026 ጀምሮ ማስረከብ እንደምንጀምር አሳውቀናቸዋል” ብለዋል።
ቦይንግ እና የደመወዝ ጭማሪ ይደረግልን የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሰራተኞች ውዝግብ ከአንድ ወር በላይ ዘልቋል።
ሰራተኞቹን ወክለው ከኩባንያው ጋር የሚደራደሩት ጆን ሆልደን ድርድሩ ረጅም ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።
ቦይንግ በ737 ማክስ አውሮፕላኖች በገጠሙ ችግሮች የኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ አየርመንገዶች ካስተናገዷቸው አደጋዎች በኋላ የምርት ጥራት ጥያቄ በስፋት እየቀረበበት ነው።
አደጋዎቹን ተከትሎ ከአንድ አመት በላይ 737 አውሮፕላኖቹ በመላው አለም ከበረራ መታገዳቸውና የተቀበላቸው ትዕዛዞች መሰረዛቸውም ለከፍተኛ ኪሳራ እንዳጋለጠው ነው የተገለጸው።
በመላው አለም 170 ሺህ ሰራተኛ ያለው ቦይንግ 10 በመቶ ወይም 17 ሺህ ሰራተኞችን በመቀነስ ከገባበት ፈታኝ ሁኔታ ለመውጣት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።