ቦሊቪያ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ያደረጉትን የሀገሪቱን ጦር መሪ በቁጥጥር ስር አዋለች
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ትላንት ምሽት የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ሙሉ ለሙሉ መክሸፉን ተናግረዋል
በትላንትናው እለት በመንግሰት ዋና ዋና መስርያ ቤቶች በር ላይ ግዙፍ ወታደራዊ ተሽከርከርካሪዎች ቆመው ታይተዋል
በቦሊቪያ የተደረገው የመፈንቅለ መንግስት ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር መዋሉን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
የሀገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል ሁዋን ጆሴ ዙኒጋ የዲሞክራሲ ግንባታ ለውጥ ያስፈልጋል በሚል በዋና ከተማዋ ላፓዝ በሚገኘኝው ቤተመንግስት ወታደሮቻቸውን አስከትለው የመፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሙከራ አድርገዋል።
ጦሩ ከቤተመንግስት ባለፈ ቁልፍ መንግስታዊ መስርያቤቶች በሚገኙበት ሙሪሎ አደባባይ ትላልቅ ወታደራዊ ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት ለመቆጣጠር ጥረት አድርጓል።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሉዊስ አርሴ ቦሊቪያዊያን መንግስታቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የሀገሪቱን ሰንድቅአላማ ይዘው ወደ ቤተ መንግስት ሲተሙ ታይተዋል።
የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ ጄነራል ዙኒጋ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት “እናት ሀገራችንን ድጋሚ እናድሳታለን” ሲሉ ተደምጠዋል።
የ12 ሚሊየን ህዝብ ባለቤት የሆነችው ሀገር ፕሬዝዳንት የትላንቱን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ አዲስ የጦር መሪ የሾሙ ሲሆን ጦሩ ወደ ካምፑ እንዲመለስ አዘዋል። ለሶስት ሰአታት ያክል ከነበረው ሂደት በኋላ ወታደሩ ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ የመንግስት መስርያቤቶች ቅጥር ግቢ ለቆ ወጥቷል።
ከጄነራሉ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጀርባ ያሉ ግለሰቦችን ለማጥራት ምርመራ የተጀመረ ቢሆንም በፕሬዝዳንት ሉዊስ እና አስተዳደራቸው ከፍተኛ ውጥረት መፈጠሩን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
ከጄነራል ዙኒጋ በተጨማሪ የባህር ሀይሉ ምክትል አድሚራል ሁዋን አርኔዝ ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ጋር በተገናኝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በቅርብ ወራት በቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሌስ እና በአሁናዊው ፕሬዝዳንት ሉዊስ አርሴ መካከል ፓርቲውን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚደረገው ፉክክር በከረረበት አጋጣሚ የተደረገው የመንግስትመገልበጥ ሙከራ በርካቶችን ተጠርጣሪ አድርጓል።
ሙከራውን ያወገዙት የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሌስ በበኩላቸው የዴሞክራሲ ሂደትን የሚያስተጓጉል እኩይ ድርጊት ሲሉ ድርጊቱን ገልጸውታል። በተጨማሪም ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራውን እንዲቃወሙ ጥሪ አድርገዋል።
በ2005 ስልጣን ላይ የነበሩት የሀገሪቱ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢቮ ሞራሊስ በላቲን አሜሪካዋ ሀገር የተሻለ ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዲመጣ ያስቻሉ መሪ ናቸው።
በ2019 የሀገሪቱ ጦር ፕሬዝዳንቱ በምርጫ ጣልቃ ሊገቡ ሲሉ ደርሸባቸዋለሁ በሚል በሀይል ከስልጣን እንዳወረዳቸው ይታወሳል።
በ2019ኙ ምርጫ ወደ ሀላፊነት የመጡት የአሁኑ ፕሬዝዳንት ሉዊስ አርሴ ሶሻሊስታዊ አስተዳደራቸው በቦሊቪያዊያን ዘንድ ተቀባይነት ባይኖረውም ዜጎች የወታደራዊ አገዛዝ ተመልሶ መምጣትን አይፈልጉም።