ጦሩ በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በባለስልጣን ጠባቂዎች እና በታጣቂዎች መካከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ መደረጉን አስታውቋል
የኮንጎ ጦር በዛሬው እለት ጧት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራን ማክሸፉን አስታውቋል።
ጦሩ እንደገለጸው በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በባለስልጣን ጠባቂዎችን እና ዩኒፎርም በለበሱ ታጣቂዎች መካከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ በርካታ የውጭ ዜጎችን ጨምሮ በድርጊቱ የተሳተፉ ወንጀለኞችን በቁጥጥር አውሏል።
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው "በኮንጎ ጦር እና በጸጥታ ኃይሎች በእንጭጩ በቁጥጥር ስር ውሏል" ሲሉ የጦሩ ቃል አቀባይ ብርጋዴረ ጀነራል ሲልቫይን ኢከንጌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
ግጭቱ የተከሰተው ከቤተመንግስት ሁለት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የባለስልጣኑ ቤት እና በርካታ ኢምባሲዎች ባሉበት ትሻትሺ ቦልቫርድ ነው ተብሏል።
ይህ ክትተት የተፈጠረው የፕሬዝደንት ፍሌክሲ ቲሽስኬዲ ፓርቲ ከፓርላማ መሪዎች ምርጫ ጋር በተያያዘ ቀውስ ውስጥ በገባባት ወቅት ነው። ምርጫው በትናንትናው እለት ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረ ቢሆንም ተራዝሟል።
ታጣቂዎቹ ጥቃት የከፈተቱት ለኮንጎ ጠቅላላ ምክርቤት አፈጉባኤነት በእጩነት በቀረቡት እና የፌደራል ህግ አውጭ በሆኑት የቪታል ካምሬህ የኪንሻሳ መኖሪያ ቤት ላይ የነበረ ሲሆን በጠባቂዎቻቸው መትረፋቸውን ቃል አቀባዩ ሚካኤል ሞቶ ሙሂማ በኤክስ ገጻቸው አስታፍቀዋል።
"የተከበሩ ቪታል ካምሬህ እና ቤተሰባቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ናቸው። የደህንነት ሁኔታው ተጠናክሯል" ሲሉ ቃል አቀባዩ አክለው ገልጸዋል።
የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዩኒፎርም ለብሰው ጥቃት የፈጸሙት ታጣቂዎች የኮንጎ ወታደሮች ናቸው ብለዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት በትሻትሺ ቦልቫርድ በተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ሁለት ፖሊሶች እና አንድ አጥቂ ተገድለዋል።
ባለፈው አርብ እለት ፕሬዝደንት ትሺስኬዲ በፓርቲያቸው ውስጥ ያጋጠማቸውን ቀውስ ለመፍታት ከፓርላማ አባላት እና የከብሔራዊ የገዥ ፓርቲ ጥምረት ጋር ውይይት አካሂደው ነበር።
ትሺስኬዲ ባለፈው ታህሳስ ወር በድጋሚ የተመረጡት ምርጫ ከፍተኛ የግልጸኝነት ጥቃቄ ተነስቶበት እንደነበር ይታወሳል።