የብራዚሉን ነውጥ ከበስተጀርባ ሆነው ይዘውሩታል የተባሉት የቀድሞ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሆስፒታል ገቡ
በብራዚል ለተነሳው ነውጥ ጣቶች ወደ ቦልሶናሮ ቢያነጣጥሩም እሳቸው ግን ተራ ውንጀላ ነው ብለውታል
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሆስፒታል የገቡት በሆድ ህመም ነው ነው ተብሏል
የብራዚሉን ነውጥ ከበስተጀርባ ሆነው ይዘውሩታል የሚባሉት የቀድሞ የብራዚል ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ሆስፒታል መግባታቸው ተሰማ፡፡
ቦልሶናሮ በኦርላንዶ፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው አድቬንት ሄልዝ ሆስፒታል የገቡት በሆድ ህመም ነው ተብሏል፡፡
የብራዚል የዜና ማሰራጫ ፖደር 360 እንደዘገበው የቀድሞ መሪው በአንጀታቸው አካባቢ ምቾት ይሰማቸው እንዳልነበር ገለጾ ሆስፒታለ የገቡት የተሟላ የህክምና ምርመራ ለማድረግ ነው ብሏል፡፡
የቀድሞ ፕሬዝዳንት እንደፈረንጆቹ በ2018 በስለት ከተወጉ በኋላ ቢያንስ ስድስት ጊዜ ሆስፒታል መግባቸውንም ጭምር አስታውሷል።
ቦልሶናሮ ሆስፒታል የገቡት በብራዚል የሚገኙ ደጋፊዎቻቸው እሁድ እለት ባነሱት ነውጥ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተወገዘ ድርጊት ከፈጸሙ በኋላ መሆኑ ነው፡፡
ነውጡ በግራ ዘመም የፖለቲካ መሪው ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የተሸነፉት ቦልሶናሮ፣ የብራዚል የኤሌክትሮኒክስ የምርጫ ስርዓት ለማጭበርበር የተጋለጠ ነው የሚለውን ክስ ማቅረባቸውን ተከትሎ እንደተቀሰቀሰ በተነገረለት ነውጥ በርካታ ውድመት መድረሱም ነው እየተነገረ ያለው፡፡
ነውጠኞቹ የሀገሪቱ ቤተመንግስት፣ ፓርላማ እና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህንጻ መቆጣጠራቸው የተሰማ ሲሆን ፤ ረብሻው ሲነሳ በሳኦ ፓውሎ ግዛት ይፋዊ ጉዞ ላይ የነበሩትን የሀገሩቱ ፕሬዝዳንት ሉላ እንጅጉን እንዳስቆጣ ይነገራል፡፡
ነውጠኞቹን “የፋሺስት ርዝራዦች” ናቸው ሲሉ የጠሩት ፕሬዝዳንቱ ፤ ፋሺስቶች በብራዚል ታሪክ ሆኖ የማያውቅ ነውር ፈጽመዋል እናም የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉም ዝተዋል።
እስካሁን 1 ሺህ 200 የሚሆኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ደጋፊዎች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር መዋላቸውም ተገልጿል፡፡
በብራዚል ለተነሳው ነውጥ ጣቶች ወደ ቦልሶናሮ ቢያነጣጥሩም ፤ እሳቸው ግን እየተነገረ ያለው ነገር ተራ ውንጀላ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ቦልሶናሮ በትዊተር ገጻቸው ላይ “በህግ መልክ የሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች የዴሞክራሲ አካል ናቸው” ሲሉም አስፍረዋል፡፡
“በስልጣን ዘመኔ በተሰጠኝ ኃላፊነት ሁሉ ሕጎችን፣ ዴሞክራሲን፣ ግልጽነትን እና የተቀደሰ ነጻነታችንን በማክበር እና በመጠበቅ በአራቱ የሕገ መንግስቱ መስመሮች ውስጥ ሁሌም (እሰራ ነበር)” ሲሉ አስምረውበታል ፕሬዝዳንቱ፤ አሁን ከነውጥ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ክስ ከእሳቸው ስብዕና ጋር የማይሄድ ፍጹም የሀሰት ውንጀላ መሆኑ በማስረገጥ፡፡
በምርጫው ከተሸነፉ በኋላ በአደባባይ ብዙም ያልተናገሩት ቦልሶናሮ የስልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ 48 ሰአታት ሲቀረው ብራዚልን ለቀው ወደ ፍሎሪዳ በማቅናታቸው በሉላ በዓለ ሲመት ላይ አለመገኘታቸው ይታወሳል፡፡
ደጋፊዎቻቸው ይህን አመጽ በሚቀሰቀስበት ወቅት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ አሜሪካ መገኘት ደግሞ ሌላው ነገሮች በጥርጣሬ እንዲታዩ ያደረግ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።