የብራዚል የቀድሞ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች የሀገሪቱ ቤተ መንግስት ተቆጣጠሩ
የብራዚሉ ነውጥ የዛሬ ሁለት ዓመት የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙትን ድርጊት የሚመሳሰል ነው ተብሏል
ፕሬዝዳንት ሉላ፤ ነውጠኞቹን “የፋሺስት ርዝራዦች ናቸው፤ የእጃቸውን ያገኛሉ” ሲሉም ዝተዋል
በቅርቡ በምርጫ ከስልጣን የተነሱት የብራዚል አክራሪው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ደጋፊዎች እሁድ እለት በፈጠሩት ነውጥ የሀገሪቱ ቤተመንግስት፣ ፓርላማ እna ጠቅላይ ፍርድ ቤት ህንጻ መቆጣጠራቸው ተሰማ።
በግራ ዘመም የፖለቲካ መሪ ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የተሸነፉት ቦልሶናሮ፣ የብራዚል የኤሌክትሮኒክስ የምርጫ ስርዓት ለማጭበርበር የተጋለጠ ነው የሚለውን ክስ ማቅረባቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸውን ለነውጥ እንዲነሳሱ መቀስቀሳቸው ይነገራል።
- ቦልሴናሮ የብራዚል ምርጫ ሽንፈትን በመቃወም ድምጹ ውድቅ እንዲደረግ እሻለሁ አሉ
- የቦልሴናሮ ደጋፊዎች ሉላ ዳ ሲልቫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ የብራዚል ጦር ጣልቃ እንዲገባ ጠየቁ
በዘህም በሺህ የሚቆጠሩ ቢጫ አረንጓዴ በለበሱ ተቃዋሚዎች በመዲናዋ ከፍተኛ ውድመት ማድራሰቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል። ነውጡ የተነሳው ሉላ ወደ ሳኦ ፓውሎ ግዛት ይፋዊ ጉዞ ላይ ከዋና ከተማው ርቀው በቆዩበት ጊዜ መሆኑም ነው የተገለጸው።
የቴሌቭዥን ምስሎች ተቃዋሚዎች ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እና የሀገሪቱ ፓርላማን ሰብረው በመግባት መፈክሮችን ሲያሰሙ እና የቤት እቃዎችን ሲሰባብሩ ያሳያሉ።
በነውጡ ወደ 3 ሺህ ሰዎች መሳተፋቸውም የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች መረጃ ያመለክታል።
የትናንቱ ነውጥ ምን አልባትም ከቀናት በፊት ቃለ መሃላ በፈጸሙት በአዲሱ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ ላይ ያነጣጠረ የመንፍቅለ መንግስት ሙከራ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
ሉላ በበዓለ ሲመታቸው ባደረጉት ንግግር በቦልሶናሮ ብሔርተኝነት ሕዝባዊነት የተበጣጠሰች ሀገርን አንድ ለማድረግ ቃል መግባታቸው አይዘነጋም።
ይህ የሉላ ንግግርም ታዲያ አክራሪ ብሄርተኛውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ሊያበሳጭ እንደሚችል ይገለጻል።
ይህ ድርጊት የዛሬ ሀለት አመት በጥር 6 ቀን 2020 የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከፈጸሙትን ድርጊት የሚመሳሰል የአክራሪ ነውጠኞች ተግባር መሆኑም እየተገለጸ ይገኛል።
ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ዓመት በፊት በጆ ባይደን መሸነፋቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው አመጽ እንዲቀሰቅሱና ኮንግረስን እንዲቆጣጠሩ አበረታተዋል በሚል በህግ ጥፋተኛ መባላቸው ይታወሳል።
በምርጫው ከተሸነፉ በኋላ በአደባባይ ብዙም ያልተናገሩት ቦልሶናሮ የስልጣን ዘመናቸው ሊጠናቀቅ 48 ሰአታት ሲቀረው ብራዚልን ለቀው ወደ ፍሎሪዳ በማቅናታቸው በሉላ በዓለ ሲመት ላይ አልተገኙም።
ደጋፊዎቻቸው ይህን አመጽ በሚቀሰቀስበት ወቅት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ አሜሪካ መገኘት ደግሞ ሌላው ነገሮች በጥርጣሬ እንዲታዩ ያደረግ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።
በተለይም በቅርቡ የቦልሶናሮ ወንድ ልጅ ኤድዋርዶ ከትራምፕ አማካሪዎች ጃሰን ሚለር እና ስቲቭ ባነን ጋር መገናኘቱን እና ምናልባትም የነውጥ ሴራው የተሰጠነሰሰው በጋራ ሊሆን ይችላል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ያም ሆኖ በብራዚል የተነሳውን ነውጥ በተመለከተ የተጠየቁት የቦልሶናሮ ቤተሰብ ጠበቃ ፍሬድሪክ ዋሴፍ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ፕሬዝዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በመግባት ይህ ተግባር ላይ የተሳተፉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውለው ጥብቅ ቅጣት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተዋል።
በዋና ከተማዋ ፕራዚሊያም ፖሊስ በሙሉ ኃይል ወጥቶ ሰላምና ጸጥታ እንዲያሰፍን ም ጠይቀዋል ፕሬዝዳንቱ።
ነውጠኞቹን “የፋሺስት ርዝራዦች” ናቸው ሲሉ የጠሩት ፕሬዝዳንቱ ፤ ፋሺስቶች በብራዚል ታሪክ ሆኖ የማያውቅ ነውር ፈጽመዋል እናም የእጃቸውን ያገኛሉ ሲሉም ዝተዋል።
እስካሁን በተወሰደው እርንጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ በነውጡ የተሳተፉ ዜጎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የብራዚሊያን ከተማን ገዥ ኢባኒየስ ሮቻ ከስልጣን እንዲነሱ ተደርጓል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጆ-ባይደንን ጨምሮ በርካታ የዓለም መሪዎች ድርጊቱን ኮንነዋል።