ኔይማር ወደ ብራዚል ብሄራዊ ቡድን ለመመለሱ እርግጠኛ አለመሆኑን ገለጸ
ብራዚል በጥሎ ማለፍ ጨዋታ በክሮሺያ ተሸንፋ ከኳታር የዓለም ውድድር መድርክ ውጪ ሆናለች
የ30 አመቱ ኔይማር ለሀገሩ 77 ጎሎችን በማስቆጣር የፔልን ሪከርድ መጋራት የቻለ ድንቅ የእግር ኳስ ጠቢብ ነው
ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማር ለብራዚል ብሄራዊ ቡድን መጫቱን ሊተው እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል፡፡
በኳታሩ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የብራዚል ቡድን በክሮሺያ ከተሸነፈ በኋላ ከብሄራዊ ቡድኑ ሊለቅ እንደሚችል የጠቆመው የፓሪስ ሴንት ዠርሜይን ኮከቡ ኔይማር፤ “በብሄራዊ ቡድን ውስጥ ምንም አይነት በር አልተዘጋም ነገር ግን ወደ ቡድኑ ስለመመለሴ 100 በመቶ ዋስትና አልሰጥም” ሲል በስሜት የታጀበው አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡
የ30 አመቱ ኔይማር ከክሮሺያ ጋር በነበረው ጨዋታ ለሀገሩ 77 ጎሎችን በማስቆጣር የብራዚላዊውን ኮከብ ፔልን ሪከርድ መጋራት የቻለ ድንቅ የእግር ኳስ ጠቢብ ነው፡፡
አርብ እለት በተደረገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ብራዚል ኔይማር ባስቆጠራት ጎል መምራት ችላ የነበረ ቢሆንም ክሮሺያዊው ብሩኖ ፔትኮቪች ጨዋታው ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ያስቀጠራት ጎል የጨዋታውን ውጤት እንዲቀየር አድርጋለች፡፡
በዚህም መደበኛውና ጭማሪ ሰአቱን በአቻ ውጤት ያጠናቀቁት ሀገራቱ ወደ ፍጹም ቅጣት ምት አምርተው ክሮሺያ 4 ለ 2 በሆነ ውጤት በማሸነፏ የእግር ኳስ ተምሳሌት እንደሆነች የሚገርላት ብራዚል ከውድድሩ ውጭ ሆናለች፡፡
ከአራት አመት በፊት በሩሲያ በተዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ብራዚል በተመሳሳይ በሩብ ፍጻሜ በቤልጂየም ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ እንደሆነች የሚታወስ ነው፡፡
እንደፈረንጆቹ 2014 ብራዚል ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫም እንዲሁ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ብግማሽ ፍጻሜ በጀርመን 7ለ 1 በሆነ አስደንጋጭ ውጤት ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ አይዘነጋም፡፡
በእነዚህ ሶስት ምእራፎች ብራዚል ያጋጠሟት ሽንፈቶች የብሄራዊ ቡድኑ አባል ለሆነው ኔይማር ከባድ እንደሆኑ ይገለጻል፡፡
በተለይም በአሁኑ ሽንፈት ስሜቱ እጅጉን የተጎዳው ኔይማር "ይህ በጣም አሳዛኝ ነው፤ የአሁኑ ስሜት ባለፈው የዓለም ዋንጫ ከተከሰተው የከፋ ነው ብዬ አስባለሁ" ሲል መናገሩም ጎል ዶት ኮም ዘግቧል፡፡
ብራዚላዊው ኮከብ ኔይማር ብራዚል ከውድድሩ ውጭ መሆኗ ቢያሳዝነውም፤ የቡድን አጋሮቹ በሜዳው ላይ ባሳዩት ተጋድሎ ኩራት እንደሚሰማው ገልጿል፡፡
በተያያዘ የብራዚል አሰልጣኝ ቲቴ ከጨዋታው በኋላ መልቀቃቸው ታውቋል ።
ቲቴ "አሳማሚ ሽንፈት ነው" ብለዋል።