በናይጀሪያ በሰርግና ቀብር ስነስርአት ላይ ያነጣጠሩ የቦምብ ጥቃቶች የበርካታ ንጹሃንን ህይወት ቀጠፉ
በቦርኖ ግዛት ሰርግ ላይ በተፈጸመ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት የተገደሉ ሰዎችን ለመቅበር ያመሩ ሰዎች ቀብር ላይ ሌላ ጥቃት ጠብቋቸዋል
የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቱን በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ቦኮሃራም ሳይፈጽመው እንዳልቀረ ተገምቷል
በናይጀሪያ በሰርግና ቀብር ስነስርአት ላይ ያነጣጠሩ የቦምብ ጥቃቶች የንጹሃንን ህይወት ቀጠፉ።
በሰሜን ምስራቅ ናይጀሪያ ቦርኖ ግዛት የደረሱት የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶች በጥቂቱ የ18 ሰዎችን ህይወት መቀማታቸውና ከ19 በላይ ሰዎች መቁስላቸው ተገልጿል።
በካሜሮን ድንበር በምትገኘው ግዎዛ ከተማ ህጻን ያዘለች እናት የተጠመደ ፈንጅ በጀርባዋ አዝላ ወደ አንድ የሰርግ ቤት በማምራት በፈጸመችው የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።
በዚህ ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቀብር በሚፈጸምበት ስፍራም ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱን የቦርኖ ግዛት የአሰቸኳይ ጊዜ አደጋ አስተዳደር አስታውቋል።
በግዎዛ ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል ላይም የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት መፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፥ የናይጀሪያው ቫንጋርድ እና ዚስ ደይ ጋዜጣ በሶስቱ ጥቃቶች የተመዘገበውን የሟቾች ቁጥር 30 አድርሰውታል።
ለአጥፍቶ መጥፋት ጥቃቶቹ እስካሁን ሃላፊነቱን የወሰደ አካል ባይኖርም በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃቶችን የፈጸመው የቦኮሃራም የሽብር ቡድን ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ቦኮሃራም ለ15 አመታት በሽምቅ በተዋጋባት የቦርኖ ግዛት ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት ማለፉንና ከ2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
ቡድኑ የግዎዛ ከተማን በ2014 ተቆጣጥሯት የነበረ ሲሆን፥ የናይጀሪያ መንግስት በወሰደው እርምጃ ከአንድ አመት በኋላ ከከተማዋ ለቆ ለመውጣት ተገዷል።
ይሁን እንጂ የሽብር ቡድኑ የሚፈጽማቸው ጥቃቶችና እገታዎች አሁንም ድረስ መቀጠላቸውን ነው ሲኤንኤን ያስነበበው።
ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይም ከአዋሳኟ ዮቤ ግዛት የቀብር ስነስርአት ፈጽመው በሚመለሱ ዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ዘገባው አውስቷል።
ቡድኖ አርሶ አደሮች ከሚሰበስቡት ምርት ላይ ግብር የሚጥል ሲሆን ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑትንም ይገድላል የሚል ክስ ይቀርብበታል።
በ2014 270 የቺቦክ ልጃገረዶችን አግቶ ከወሰደ በኋላ የጭካኔና ሽብርተኝነት ስሙ የናኘው ቦኮሃራም በናይጀሪያ ጦር ጥቃት አቅሙ ቢዳከምም ንጹሃን ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸሙን አላቋረጠም።
የቡድኑ ስጋትነት ከናይጀሪያ አልፎ ወደ ኒጀር፣ ካሜሮን እና ቻድ በመስፋፋቱም ሀገራቱ ሽብርተኛውን ቡድን ለመዋጋት የጋራ ወታደራዊ ጥምረት መመስረታቸው የሚታወስ ነው።