ቦሪስ ጆንሰን ህግን ጥሰው በመቀጣታቻው ስልጣን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ነው
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በፖሊስ የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት መክፈላቸውን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን እና የፍይናንስ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ ጨምሮ ሌሎችም የስራ ኃላፊዎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ተከትሎ የተጣለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ተላልፈው በመገኘታቸው ነው በፖሊስ የተቀጡት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግስት በተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ውስጥ የተዘጋጀ የልደት ድግስ ላይ በመገኘታቸው የተቀጡ ሲሆን፤ በዚህም ቦሪስ ጆንሰን በስልጣን ላይ እያሉ ህግ ጥሰው የተቀጡ የመጀመሪያው የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል።
ይህንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን በቴልቭዥን በሰጡት መግለጫ፤ “በፖሊስ የተጣለብኝን ቅጣት ከፍያለሁ፤ ሙሉ በሙሉ የቅርታ እንዲደረግልኝ እጠይቃለሁ” ብለዋል።
የፍይናንስ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ በድግሱ ላይ በመገኘታቸው ቅጣቱ የተላለፈባቸው መሆኑንም ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን እና የፍይናንስ ሚኒስትሩ ሪሺ ሱናክ ህግ ተላልፈው በመገኘታቸው እና በፖሊስ መቀጣታቸውን ተከትሎም ስልጣናቸውን እንዲለቁ ግፊት እየተደረገባቸው ይገኛል።
ሆኖም ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፍይናንስ ሚኒስትሩ የስልጣን ልቀቁ ጥያቄውን እንደማይቀበሉ በመግለፅ ስራቸውን መቀጠላቸው ተነግሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን እና የፍይናንስ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ በፖሊስ በገንዘብ ስለመቀጣታቸው እንጂ ምን ያክል የገንዘብ ቅጣት እንደተላለፈባቸው በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።
የብሪታኒያ ፖሊስ የኮቪድ 19 ክልከላን ተላለፈው የተሰባሰቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የቀጣ ሲሆን፤ ቅጣቱም ከ78 ዶላር እስከ 13 ሺህ ዶላር መካከል መሆኑ ተነግሯል።