በብሪታንያ አውሮፕላን ማረፊያዎች አነፍናፊ ውሾች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት ሊጀምሩ ነው
የአነፍናፊ ውሾቹ በኮሮና የተያዘን ሰው የመለየት አቅም 94.3 በመቶ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ነው ተብሏል
አነፍናፊ ውሾቹ መንገደኞች ምልክት ከማሳየታቸው በፊትም ቢሆን መለየት የሚችሉ መሆኑ በጥናቱ ተመላክቷል
በብሪታንያ በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ የአየር መንገድ አነፍናፊ ውሾች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ መንገደኞችን መለየት ሊጀምሩ መሆኑ ታውቋል።
የብሪታንያ ተመራማሪዎች በዛሬው እለት እንዳስታወቁት ስልጠና በወሰዱ የፖሊስ አነፍናፊ ውሾች አማካኝነት በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ልየታ በቅርቡ ይጀመራል።
አነፍናፊ ውሾች በኮሮና የተያዙ ሰዎች ካልሲን እንዲያሸቱ በማድረግ ስልጠና መውሰዳቸውንም ነው ተመራማሪዎቹ ያስታወቁት።
አነፍናፊ ውሾቹ በቅርቡ በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት እንዲጀምሩ እንደሚደረግትም ገልጸዋል።
ተመራማሪዎቹ ስልጠና የወሰዱ አነፍናፊ ውሾች በግማሽ ሰዓት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በማሽተት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት እንደሚችሉም አረጋግጠዋል።
አነፍናፊ ውሾች በኮሮና ቫይረስ የተያዘን ሰው የመለየት አቅም 94.3 በመቶ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መሆኑንም ነው የገለጹት።
ተመራማሪዎቹ ጥናቱን በሚያካሂዱበት ወቅት 3 ሺህ 500 ከዚህ ቀደም በኮሮና ቫይረስ ተይዘው የነበሩ ሰዎችን ያልታጠቡ ቲ-ሸርቶች እና ካልሲዎችን መጠቀማቸውንም አስታውቀዋል።
ሙከራውም አነፍናፊ ውሾቹ መንገደኞች ምልክት ከማሳየታቸው በፊትም ቢሆን መለየት የሚችሉ መሆኑንም ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል።