ቦሪስ ጆንሰን ዳግም ለብሪታኒያ ጠቅላይ ሚንስትርነት እንደሚወዳደሩ ተገለጸ
ቦሪስ ጆንሰንን ተክተው ጠቅላይ ሚንስትር ሊዝ ትሩስ ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸው ይታወሳል
ሪሺ ሱናክ፣ ሞርዳንት እና ቤን ዋላስ የቦሪስ ጆንሰን ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል
የብሪታንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ዳግም ለጠቅላይ ሚንስትርነት እንደሚወዳደሩ ተገለጸ።
የቀድሞው ጋዜጠኛ እና የለንደን ከንቲባ የነበሩት ቦሪስ ጆንሰን ቴሬዛ ሜይን በመተካት ብሪታንያን ከፈረንጆቹ 2019 እስከ አሳለፍነው ነሀሴ ወር ጠቅላይ ሚንስትር ነበሩ።
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣውን ህግ ተላልፈዋል፣ ይዋሻሉ እና ሌሎች ያልተገቡ ባህሪያት አሏቸው በሚል የሀገሪቱ ምክር ቤት አባላት ጫና አሳድረውባቸው ስልጣን ለመልቀቅ ተገደውም ነበር።
ይሄንን ተከትሎም የ50 ዓመቷ ሊዝ ትሩስ ከሌሎች እጩዎች ጋር በመወዳደር እና አብላጫ ድምፅ በማግኘት ከመስከረም ጀምሮ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ።
ይሁንና በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በዋጋ ግሽበት እየተፈተነ ያለውን የብሪታንያ ኢኮኖሚ ለማረጋጋት እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ስልጣን ከያዙ በኋላ በወሰዷቸው እርምጃዎች የብሪታንያ መገበያያ ገንዘብ ፓውንድ ስተርሊንግ ከዶላር እና ዩሮ አንጻር አቅሙ መዳከሙ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ቀውስ አስከትሏል።
ይሄንን ተከትሎም ጠቅላይ ሚንስትሯ በደረሰባቸው ጫና ስልጣናቸውን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ እንደምያስረክቡ አስታውቀዋል።
ሊዝ ትሩስ በብሪታንያ መሪ ታሪክ ለአጭር ቀናት ብሪታንያን በመምራት የመጀመሪያዋ የሆኑ ሲሆን እሳቸውን ለመተካት እጩዎች ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ከአራት ወር በፊት ስልጣን የለቀቁት ቦሪስ ጆንሰን እንዲመለሱ በርካታ ብሪታንያዊያን በትዊተር ቦሪስ ይመለስ የሚል ዘመቻ ጀምረዋል።
ይሁንና የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር በስልጣን ዘመናቸው አሳይተውታል የተባለው ምርመራ አለመጠናቀቁ በቀላሉ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዳይመለሱ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል።
ከቦሪስ ጆንሰን በመቀጠል የቀድሞው የብሪታንያ ፋይናንስ ሚንስትር እና የሊዝ ትሩስ ተቀናቃኝ የነበሩት ሪሺ ሱናክ እንዲሁም የቀድሞው የብሪታንያ መከላከያ ሚንስትር ቤን ዋላስ እና ሙርዶንት የቦሪስ ዋነኛ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ተገልጿል