ቦሪስ ጆንሰን፤ ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ከለቀቁ በኋላ ሚሊየነር ሊሆኑ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች
አሁን ግን ከመጽሃፍ ሽያጭ፣ ንግግር ከማድረግ እና ከመጻፍ ሚሊየን ፓውንዶችን ሊያገኙ እንደሚችሉ ተነግሯል
ጆንሰን ስልጣን ላይ ሳሉ ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ሳይጨምር 164 ሺ ፓውንድ ነበር አመታዊ ደሞዛቸው
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸው ይታወሳል፡፡
ጆንሰን ስልጣን የሚለቁት የካቢኔ አባሎቻቸው ጭምር ስልጣናቸውን በመለቀቅ ባሳደሩባቸው ጫና ነው፡፡ እርሳቸውን ለመተካትም የካቢኔ አባላቶቻቸውን ጨምሮ 11 ገደማ ፖለቲከኞች በእጩነት መቅረባቸው ተነግሯል፡፡
የቀድሞው ጋዜጠኛ ስልጣን መልቀቅ ግድ ቢሆንባቸውም ሚሊየነር ሆነው የሚለቁበት አጋጣሚ እንዳለ ነው የሚነገረው፡፡
ጆንሰን ስልጣን ላይ ሳሉ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር 164 ሺ ፓውንድ ነበር አመታዊ ደሞዛቸው፡፡ ይህ ከከፍተኛ ተከፋይ የዓለማችን መሪዎች ተርታ ያሰለፋቸዋል፡፡ ሆኖም አሁን ከስልጣናቸው ከወረዱ በኋላ ሊያገኙ የሚችሉት በሚሊየኖች የሚቆጠር ገቢ ይህን የሚያስንቅ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው፡፡
ስልጣናቸውን በይፋ ከለቀቁ በኋላ ሊጻፍ እንደሚችል ከሚጠበቀው የማስታወሻ መጽሃፋቸው፣ ሊያደርጓቸው ከሚችሉ ንግግሮች እና በተጋባዥነት ሊቀርቡ ከሚችሉባቸው የቴሌቪዥንና ሌሎች የብዙሃን መገናኛ ፕሮግራሞች በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብን ሊያጋብሱ እንደሚችሉ ነው የሚጠበቀው፡፡
ልክ ቀደም ሲል ሲያደርጉት እንደነበረው ሁሉ አምደኛ ሆነው ሊጽፉ ከሚችሉባቸው ስመ ጥር ጋዜጦች የተሻለ ክፍያን ሊያገኙ እንደሚችሉም ይጠበቃል፡፡
ከ1990ዎቹ አጋማሽ ወዲህ ብሪታኒያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉ ፖለቲከኞች እያንዳንዳቸው በእንዲህ ዐይነት መንገድ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ሚሊየኖችን አጋብሰዋል፡፡ ነገር ግን ጆንሰን ከቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ካገኙት 100 መሊዮን ፓውንድ የበለጠ ገንዘብን ሊያገኙ እንደሚችሉ ነው እየተጠበቀ ያለው፡፡
ቀለል ያሉና ተጫዋች እንዲሁም ጥሩ ጸሃፊ እንደሆኑ ከሚነገርላቸው ቦሪስ ጆንሰን ጋር ስምምነትን ለማድረግ ኔትፍሊክስ የተባለውን ታዋቂ የአሜሪካ የፊልም ኩባንያ ጨምሮ ሌሎች እየተፎካከረሩ እንደመገኙም ተነግሯል፡፡
ለሶስት ዓመታት የዘለቀውን የጆንሰንን የስልጣን ዘመን ማስታወሻ ለመጻፍም ተቋማት በመሽቀዳደም ላይ ናቸው፡፡ ይህ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ካገኙት 800 ሺ ፓውንድ የተሻለ ክፍያን እንደሚያስገኝላቸው ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ጆንሰን፤ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራካ ሁሴን ኦባማ ሁለት ማስታወሻዎቻቸው ሲጻፉ ካገኙት 65 ሚሊዮን ዶላር የበለጠ ሊያገኙ አይችሉም ተብሏል፡፡
የዴይሊ ቴሌግራፍ አምደኛ የነበሩት የቀድሞው የለንደን ከንቲባ ጸሃፊና ደራሲ ቦሪስ ጆንሰን በሳምንት ለሚጽፉት አንድ መጣጥፍ (አርቲክል) 275 ሺ ፓውንድ ይከፈላቸው ነበር፡፡ አሁን ግን ሊኖራቸው ከሚችለው መረጃ እና ታዋቂነት አንጻር ከዚህ በእጅጉ የተሻለ ክፍያን እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ነው፡፡
አዋዝቶ መናገር የሚችሉበትን ርትዑ አንደበት መታደላቸውም የቀድሞዋ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ ካደረጓቸው ንግግሮች ካገኙት 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ፓውንድ የበለጠ ገቢን እንደሚያስገኝላቸውም ይጠበቃል ተብሏል፡፡
ጆንሰን ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በአንድ መድረክ ንግግር ለማድረግ እስከ 450 ሺ ፓውንድ የሚደርስ ክፍያን ተቀብለዋል፡፡ አሁንም በብሪታኒያ ንግግር ለማድረግ የሚጋበዝ አንድ ታዋቂ ሰው ከ150 ሺ ፓውንድ በላይ ያገኛል፡፡
በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ጆንሰን ከስልጣን መልቀቅ በኋላ ሚሊየነር እንደሚሆኑ ነው የዘ ናሽናል ዘገባ የሚያትተው፡፡