ድምጽ ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ የሄዱት የቀድሞ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር መታወቂያ ረስተው ለመመለስ ተገደዋል ተብሏል
በብሪታንያ ያለመታወቂያ መምረጥ እንዳይቻል ሲቀሰቅሱ የነበሩት ቦሪስ ጆንሰን መታወቂያ ረስተው ተገኙ፡፡
የቀድሞው የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከዚህ በፊት መራጮች ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ሲመጡ ማንነታቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ይዘው እንዲገኙ የሚያስገድድ ህግ እንዲዘጋጅ ሲቀሰቅሱ ነበር፡፡
የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽንም ይህን ህግ አስገዳጅ እንዲሆን ያደረገ ሲሆን ከሰሞኑ እየተካሄደ ባለው የአካባቢያዊ ምርጫ ላይ ራሳቸው ቦሪስ ጆንሰን መታወቂያ ረስተው መገኘታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቦሪስ ጆንሰንም በደቡባዊ እንግሊዝ ኦክስፎርድሻየር ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ለመምረጥ ሲሞክሩ መምረጥ እንደማይችሉ ከተነገራቸው በኋላ ተመልሰው መታወቂያቸውን አሳይተው እንደመረጡም ተገልጿል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ በብሪታንያ መራጮች ከዚህ በፊት ስማቸውን ብቻ እየተናገሩ ድምጽ መስጠት ይችሉ የነበረ ሲሆን አሁን ግን መራጮች ማንነታቸውን የሚገልጹ መታወቂያዎችን መያዝ እንደ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
መራጮች መታወቂያ መያዝ እንደ ግዴታ የተጣለባቸው የምርጫ ድምጽ ማጭበርበሮችን ለማስቀረት ነውም ተብሏል፡፡
ብሪታንያ የኢትዮጵያ አበባ ያለ ግብር ወደ ሀገሯ እንዲገባ ፈቀደች
ቦሪስ ጆንሰን በብሪታንያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ ሲሆኑ ከ2019 ጀምሮ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው የተመረጡ ቢሆንም ከሁለት ዓመት በኋላ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተሰነዘሩባቸው ወቀሳዎች ምክንት ስልጣን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
የቀድሞው ጋዜጠኛ ቦሪስ ስልጣን ከለቀቁ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ቀድሞ ስራቸው የተመለሱ ሲሆን አሁን ላይ ዴይሊ ሜይል ለተሰኘው ጋዜጣ አምደኛ ሆነው እየጻፉ ይገኛሉ፡፡