“ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችም ሆኑ ሸማቂ ኃይሎች ታጥቀው እንዳይንቀሳቀሱ ይደረጋል”-ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ
የሁለቱን ምክር ቤቶች 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን በይፋ አስጀምረዋል
የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብም ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል
“ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችም ሆኑ ሸማቂ ኃይሎች ታጥቀው እንዳይንቀሳቀሱ ይደረጋል”-ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ
በተያዘው ዓመት “ማንኛውም ኢ-መደበኛ አደረጃጀትም ይሁን ሸማቂ ኃይል ትጥቅ ይዞ እንዳይንቀሳቀስ” ለማድረግ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ አስታወቁ፡፡
ፕሬዚዳንቷ 5ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ ዓመት የስራ ዘመንን ዛሬ ከሰዓት በኋላ በይፋ ከፍተዋል፡፡
የመንግስትን ተቀዳሚ ዕቅዶች ባስተዋወቁበት የመክፈቻ ንግግራቸው የተጠናቀቀው ዓመት በርካታ ታሪካዊ ሊባሉ የሚችሉ ድሎች የተመዘገቡበት ዓመት ነበር ብለዋል፡፡
ሆኖም “ምርቅ እና ፍትፍት” ነበር ያሉት ፕሬዚዳንቷ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከገጠሙ ሃገራዊ ችግሮች ባሻገር የዜጎች ህይወት የተቀጠፈበት በርካቶች የተጎዱበት እና የተፈናቀሉበት እንደነበር አልሸሸጉም፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ነገር በለውጥ ሂደት ውስጥ ሊያጋጥም የሚችል ቢሆንም ህዝብ ባሳየው ትዕግስትና አስተዋይነት የሃገር ህልውና አደጋ ላይ ሳይወድቅ ቀርቷል ብለዋል ለተስተዋለው ታጋሽነት በማመስገን፡፡
ዴሞክራሲው በስሜትና ጉልበት ተጽዕኖ ስር ወድቆ ነበር ነው ፕሬዝዳንቷ ያሉት፡፡
ይህ ዜጎችን ለከፋ ስቃይና እንግልት የዳረገው ችግር ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን በተወሰዱ እርምጃዎች ሃገርና ህዝብን ለመታደግ መቻሉንም ገልጸዋል፡፡
ያጋጠሙን የህግ ጥሰቶች የዴሞክራሲ አረዳዳችንን ያሳዩ ናቸውም ያሉም ሲሆን ዴሞክራሲ በፍላጎት ብቻ ሳይሆን በሆደ ሰፊነት፣ በአስተዋይነት እና በቁርጠኝነት ዋጋ ተከፍሎበት ጭምር እንደሚገነባ እና ከፍተኛ ኃላፊነትን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡
ዓመቱ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሌሎች ዴሞክራሲን በባዶ ከመሻት ባለፈ የሚጠይቀውን ዲሲፕሊን እንዲላበሱ እና በህግ የበላይነት እንዲመሩ ለማድረግ የሚሰራበት እንደሚሆንም ነው የተናገሩት፡፡
ለዚህም 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ከቀደሙት ሃገራዊ ምርጫዎች በተሻለ ችግሮችን በሚያርም እና የህዝብን የዴሞክራሲ ጥማት በሚያረካ መልኩ ይካሄዳል ያሉ ሲሆን አስተማማኝ ሰላምን ለመገንባት ህዝብን ባሳተፈ መልኩ ይሰራል ብለዋል፡፡
ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ እንቅፋት የሆኑ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችም ሆኑ ሸማቂ ኃይሎች ታጥቀው እንዳይንቀሳቀሱ እንደሚደረግም ፕሬዚዳንት ሣህለ ወርቅ አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ ብሔሯ የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ ባለመሆኑ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን የማጠናከር ሥራ ይሰራል የሲቪል ሰርቪስ የአገልግሎት ስርዓቱ በዲጅታል ስርዓት ይታገዛልም ብለዋል፡፡