ክልከላው የግድቡን ደህንነት መጠበቅ እንደሆነ ተገልጿል
ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ አካባቢ ማንኛውንም የአየር በረራ ከለከለች
በታላቁ ህዳሴ ግድብ አካባቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ የአየር ክልል ለማንኛውም የአየር በረራ ዝግ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ግድቡ በሚገኝበት አካባቢ ምንም አይነት በረራ ማድረግ አይቻልም፡፡
ይሁንና ከሚመለከተው የመንግሥት የደህንነት አካል በሚሰጥ ልዩ ፈቀድ ክልከላው በተጣለበት አካባቢ በረራ የሚፈቀድላቸው ሊኖሩ እንደሚችሉም ኮሎኔል ወሰንየለህ ተናግረዋል፡፡
ውሳኔው የግድቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተላለፈ ሲሆን በዚሁ ጉዳይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡ ውሳኔው ተግባራዊ ከተደረገ ጥቂት ወራት እንደተቆጠሩም ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በቅርቡ የመጀመሪያ ዙር የዉሃ ሙሌቱ የተጠናቀቀው የህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት መካከል ያለመግባባት ምንጭ ሆኖ የቆየ ሲሆን በተለይ ግብፅ እና ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ የተካረረ አቋም ይዘዋል፡፡ ከሁለቱ ሀገራት በተጨማሪ ሱዳንን ያካተተ የሦስትዮሽ ድርድር ለረጅም ጊዜ ሲካሔድ ቢቆይም እስካሁን ድረስ የመጨረሻ እልባት አልተገኘለትም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሦስቱ ሀገራት በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡