ቦትስዋና እስራኤልና ፍልስጤም የቆየ አለመግባባት ውስጥ በመሆናቸውና ጉዳዩ ቀላል ስላልሆነ ሁሉም የህብረቱ አባል ሀገራት ሊያውቁት ይገባ ነበር ብላለች
የቦትስዋና የአለምአቀፍ ጉዳዮችና ትብብር ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ህብረቱ ውሳኔ ከማሳለፉ በፊት፣ ጉዳዩ ቀላል ስላልሆነ እና በተለይም እስራኤልና ፍልስጤም የቆየ አለመግባባት ውስጥ በመሆናቸው ሁሉም የህብረቱ አባል ሀገራት ሊያውቁት ይገባ ነበር ብላለች፡፡
መግለጫው እስራኤል በፍልስጤም እየፈጸመች ያለችው ቀጣይነት ያለው የሰፈራ ፐሮግራም ከአፍሪካ ህብረት መተዳደሪያ ደንብ ውጭ ስለሆነ፣የህብረቱን ውሳኔ እንደማትቀበል ጠቅሷል፡፡ ቦትስዋና የእስራኤልን ወረራ እንደምትቃወምና ለፍልስጤም ያላትን ድጋፍና አጋርት እንምትቀጥል አስታውቃለች፡፡
እስራኤል ባለፈው ሳምንት ነበር በህብረቱ የታዛቢነት ቦታ ያገኘችው፡፡ የአፍሪካ ህብረት አንድነት ድርጅት ፈርሶ ወደ አፍሪካ ህብረት እስከተቀየረበት ጊዜ ድረስ እስራኤል የታዛቢነት ቦታ ነበራት፡፡ እስራኤል ከ46 የአፍሪካ ሀገራት ጋር ግንኙነት በመመስረት የንግድና የትብብር ስራዎችን እያስፋፋች ነው፡፡
ቦትስዋና የህብረቱን ውሳኔ በመቃወም ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ ሀገር ሆናለች፡፡በተመሳሳይ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ህብረቱ ለእስራኤል የታዛቢነት ቦታ የሰጠበት መንገድ አግባብ አለመሆኑንና ሁሉም አባል ሀገራት ሊመክሩበት የሚገባ ጉዳይ እንደነበር ማስታወቋ ይታወሳል፡፡