በፓሪስ ኦሎምፒክ በጾታዋ ምክንያት መነጋገርያ የሆነችው አልጄርያዊት ቦክሰኛ ወደ ፍጻሜው አለፈች
ኢማን ከሊፍ በምሽቱ ጨዋታ ታይላንዳዊቷን ተፎካካሪዋን በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ወደ ሚያስገኝው የፍጻሜ ውድድር አልፋለች
ታይላንዳዊቷ ቦክሰኛ ከውድድሩ በኋላ የኢማን ፍጥነት እና ጥንካሬ የሚስገርም ነው ብላለች
የ25 አመቷ አልጄሪያዊት ቦክሰኛ ኢማን ከሊፍ በፓሪሱ ኦሎምፒክ ወደ ፍጻሜው ማለፏን አረጋገጠች፡፡
በውድድሩ የመጀመሪያ ግጥሚያ ጣሊያናዊቷን ተፎካካሪ በ46 ሰከንድ በበቃኝ ያሸነፈችው ኢማን ካሊፍ በጾታዋ ሁኔታ ዙርያ በውድድሩ መነጋገርያ ሆና መቆየቷ ይታወቃል፡፡
በምሽቱ ግጥሚያ ከታይላንዳዊቷ ጃንጄም ሱዋንፌንግ ጋር የተገናኘችው ኢማን በዳኞች ውሳኔ ነው ግጥሚያውን አሸነፍ ለፍጻሜው የበቃችው፡፡
ሱዋንፌንግ ከግጥሚያው በኋላ በሰጠችው አስተያየት የኢማን ቦክስ ጥንካሬ እና ፍጥነቱ አስገራሚ እንደሆነ ተናግራለች፡፡
በመጀመሪያው ዙር በሁለቱም እጆቿ የምትሰነዝራቸው ቡጢዎች ለመከላከል እንኳን እድል የማይሰጡ እንደነበሩ ተፎካካሪዋ መስክራላታለች፡፡
በኢማን ምክንየት በየቀኑ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረባቸው የሚገኝኙት አወዳዳሪዎቹ የኢማንን ሴትነት ለማረጋገጥ ምርመራ እንዲያደርጉ እና ከውድድሩ እንድትሰረዝ ጫና ቢደርስባቸውም እስካሁን የተለየ ማጣርያ አላደረጉም፡፡
አወዳዳሪዎቹ በሰጡት ምላሽ በሰውነቷ ውስጥ የሚገኝው የቴስቴስትሮን መጠን በውድድሩ በሴት ምድብ ውስጥ እንዳትወዳደር የሚከለክላት አይደለም ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ማርክ አዳምስ ተወዳዳሪዋ የተወለደችውም ሆነ የኖረችው ሴት ሆና ነው፤ አንዳንዶች እንደሚሉት ከጾታ ቅያሪ (ትራንስጀንደር) ጋር የሚያገናኝው ምንም ነገር የለም ነው ያሉት፡፡
ባለፈው አመት በተካሄደው የሴቶች አሸናፊዎች አሸናፊ የቦክስ ውድድር አለም አቀፉ የቦክስ አሶሴሽን ኢማን የወንድ ጾታን የሚያሳየው ኤክስ ዋይ ክሮሞዞም ተገኝቶባታል በሚል ከውድድሩ አግዷት ነበር፡፡
የፓሪሱን ኦሎምፒክ ውድድር ጨምሮ ተከታታይ 12 ግጥሚያዎችን ማሸነፍ የቻለችው ኢማን በመጪው አርብ በሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ የወርቅ ሜዳልያንውን ልትወስድ እንደምትችል ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
ሰዎች ስለእኔ የሚያወሩት አያስገርመኝም ያለችው ኢማን ትኩረት የማደረግው በውድድሩ ሀገሬ የሚገባትን ክብር ለማጎናጸፍ ነው ብላለች፡፡
ላለፉት ስምንት አመታት የቦክስ ውድድሮችን ስታደረግ የቆየችው ኢማን ከአራት ዓመታት በፊት በተደረገው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ነበረች።
በወቅቱም በ60 ኪሎግራም ቀላል ክብደት የውድድር መደብ በሩብ ፍጻሜው በአየርላንዷ ኬሊ ሃሪንግተን አምስት ለ ዜሮ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ ሆናለች።
ኢማን በመጪው አርብ ከቻይናዊቷ ንግ ሊዩ ጋር ለወርቅ ሜዳሊያው ትፋለማለች፡፡