የቀድሞው የአለም ቦክስ ሻምፒዮና ማይክ ታይሰን ሊያደርገው የነበረው የቦክስ ፍልሚያ ተራዘመ
በማይክ ታይሰን እና በዩትዩበሩ ጄክ ፖውል መካከል ይደረጋል የተባለው ፍልሚያ ለሰኔ 20 ቀጠሮ ተይዘለት ነበር
ተጠባቂው የቦክስ ፍልሚያ ማይክ ታይሰን በጋጠመው መጠነኛ ህመም ምክንያት መራዘሙ ተሰምቷል
የቀድሞው የአለም ቦክስ ሻምፒዮና ማይክ ታይሰን ከ19 አመታት በኋላ ወደ ‘’ሪንግ’’ የሚመለስበት ተጠባቂው የቦክስ ግጥሚያ ታይሰን ባጋጠመው የሆድ ህመም መራዘሙ ተሰምቷል።
ባጋጠመው ህመም በሙሉ አቅሙ ልምምዱን እያከናወነ እንዳልሆነ የገለጸው ማይክ ታይሰን ዶክተሮቹ ለትንሽ ሳምንታት እረፍት እንዲያደርግ እና ቀለል ያሉ ልምምዶችን ብቻ እንዲሰራ እንዳሳሰቡት አስታውቋል።
በ1990ዎቹ ከምገኝበት በተሸለ አቋም ላይ እገኛለሁ ያለው ታይሰን በቅርቡ ወደ ሙሉ ልምምዱ እንደሚመለስ ነው ይፋ ያደረገው።
ተፋላሚው የ27 አመቱ ጄክ ፓውል ማይክ ታይሰን ጤናውን ለመንከባከብ የሚወስደው ግዜ ምክንያታዊ መሆኑን ገልጾ ፍልሚያው በመራዘሙ አለመከፋቱን ተናግሯል።
ተጋጣሚዎች ፍትሀዊ የሆነ የልምምድ ግዜ እንዲኖራቸው እና ሁለቱም ለውድድሩ ዝግጁ እና ብቁ በሆኑበት ግዜ ብቻ ውድድሩን ለማካሄድ ተስማምተዋል።
የተወዳዳሪዎቹ ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ነው ያሉት የውድድሩ አዘጋጆች ውድድሩ የሚካሄድበትን ግዜ በቀጣዩ ሳምንት እንደሚያስታውቁ ተናግረዋል።
ፍልሚያው በአርሊንግተን ቴክሳስ 80 ሺህ ሰዎች በሚይዝ ስታድየም ውስጥ እንደሚደረግ የተነገረ ሲሆን፣ በተጨማሪም ግዙፉ የፊልም እና መዝናኛ ማሰራጫ ኔትፍሊክስ ውድድሩን ለማስተላለለፍ እየተጠባበቀ ይገኛል።
የ57 አመቱ ማይክ ታይሰን በአለም ላይ በቦክሱ ዘርፍ ስመጥር ከሆነ ስኬታማ ቦክሰኞች መካከል አንዱ ሲሆን ሶስት የተለያዩ የቦክስ ፍልሚያ ክብሮችን በመቀዳጀት የመጀመርያው የከፍተኛ ሚዛን ቦክሰኛ ነው።
በ1990 በበስተር ዳግላስ ተሸንፎ ከቦክስ አለም እራሱን ያገለለው ታይሰን አነስተኛ የቦክስ ፍልሚያዎችን ሲያደረግ ቆይቷል ለመጨረሻ ግዜ የቦክስ ግጥምያ ያደረገው በ2005 በተከናወነ የቦክስ ኤግዝቢሽን ላይ ሲሆን አሁን ወደ ሪንግ የሚመለሰው ከ19 አመታት በኋላ ነው።
ተፋላሚው ጄክ ፖውል በበኩል ከማይክ ታይሰን በ30 አመት የሚያንስ የ27 አመት ወጣት ዩትዩበር ነው፡፡ ወደ ቦክስ ውድድሩ አለም ከገባ በኋላ ከቀድሞ የዩኤፍሲ ተጋጣሚዎች ጋር 10 ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኙን ማሸነፍ ችሏል።