ሀገራት በፓሪስ ኦሎምፒክ ሜዳልያ ለሚያመጡ አትሌቶቻቸው ምን ለመሸለም ቃል ገብተዋል?
ፖላንድ ወርቅ ለሚያገኙ አትሌቶቿ 63 ሺህ ዶላር እና ባለሁለት ክፍል አፓርታማ ለመሸለም ቃል ገብታለች
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ሜዳልያ የሚያስገኙ ስፖርተኞች ከአስገዳጅ ብሄራዊ ውትድር አገልግሎት ውጭ ይሆናሉ ብላለች
ከ200 በላይ ሀገራትን የወከሉ ከ10 ሺህ በላይ አትሌቶች እየተሳተፉበት የሚገኘው የፓሪስ ኦሎምፒክ ዛሬ 11ኛ ቀኑን ይዟል።
አሜሪካ እና ቻይና እየመሩት በሚገኘው የሜዳልያ ሰንጠረዥ 66 ሀገራት ተካተዋል።
ሀገራት በ33ኛው ኦሎምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶቻቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት ልክ ያዘጋጁትን ሽልማት ይፋ አድርገዋል።
አብዛኞቹ ሽልማቶች የገንዘብ ቢሆኑም በገንዘብ የማይተመኑና ልዩ ሽልማቶችን የሚሰጡ ሀገራትም አሉ።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በፓሪስ የወርቅ፣ ብር እና የነሃስ ሜዳልያ ለሚያገኙ አትሌቶቻቸው የተለየ ሽልማት የሚሰጡ ሀገራትን ይዞ ወጥቷል።
ደቡብ ኮሪያ
ሴኡል በፓሪስ ሜዳልያ የሚያስገኙ ስፖርተኞች (ከወርቅ እስከ ነሃስ) ከአስገዳጅ ብሄራዊ ውትድር አገልግሎት ውጭ ይሆናሉ ብላለች።
ሙሉ አካል ያላቸው ደቡብ ኮሪያውያን ወንዶች በሙሉ እስከ 28 አመታቸው ድረስ ለ18 ወራት በብሄራዊ ውትድርና መሳተፍ ይገደዳሉ።
በኦሎምፒክ ሜዳልያ የሚያመጡት ግን ከዚህ አስገዳጅ ብሄራዊ ውትድርና ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል።
ፖላንድ
በፓሪስ ኦሎምፒክ ወርቅ የሚያገኙ ፖላንዳውያን አትሌቶች 63 ሺህ የአሜሪካ ዶላር፣ ሁለት ክፍል አፓርታማና አልማዝ ይሸለማሉ።
የብር እና ነሃስ ሜዳልያ የሚያመጡትም የገንዘብና ሌሎች ሽልማቶች ቃል ተገብቶላቸዋል።
ኢንዶኔዥያ
የደቡብ እስያዊቷ ሀገር ኢንዶኔዥያ የኦሎምፒክ ሜዳልያ ለሚያመጡ አትሌቶቿ ከላሞች እስከ ቤቶች ሽልማቶችን ትሰጣለች።
በፓሪስ ኦሎምፒክ ሰንደቋን ከፍ ለሚያደርጉት ስፖርተኞች ቤት መስሪያ ቦታ ተዘጋጅቶላቸዋል የተባለ ሲሆን፥ የሀገሪቱ ቱሪዝም ሚኒስቴር በአምስት የቱሪስት መዳረሻዎች ሙሉ ወጪያቸውን ሸፍኖ ለማንሸራሸር ቃል ገብቷል።
ዮርዳኖስ
አትሌት አህማድ አቡ ጉአሽ በቴኳንዶ ለዮርዳኖስ የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ ሜዳልያ በሪዮ ኦሎምፒክ ሲያስገኝ የሀገሪቱ ኦሎምፒክ ኮሚቴ 140 ሺህ ዶላር ሸልሞት ነበር።
ንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ ልዩ ክብር የሚሰጠውን ሽልማት ያበረከቱለት ሲሆን፥ የመኪና አምራቾችና እና ሌሎች ኩባንያዎችም ስጦታ አበርክተውላታል።
በኦሎምፒክ መድረክ ለ12ኛ ጊዜ እየተሳተፈ ለሚገኘው የዮርዳኖስ ልኡክ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ቃል ተገብቶለታል ተብሏል።
ኢራቅ
የኢራቅ የኦሎምፒክ እግርኳስ ቡድን በፓሪስ በመሳተፉ ብቻ ለእያንዳንዱ ተጫዋች 9 ሚሊየን ዲናር (7 ሺህ 200 ዶላር) ሸልማለች።
ቤት መስሪያ ቦታ እና የመኪና ስጦታም ተበርክቶላቸዋል።
ቡድኑ የብር ወይንም የወርቅ ሜዳልያ ቢያገኝ ለተጫዋቾቹ ከ500 ሺህ ዶላር በላይ ለመስጠት ቃል ተገብቶ ነበር።
ማሌዥያ
በፓሪስ ለማሌዥያ ሜዳልያ የሚያስገኝ አትሌት አመቱን ሙሉ አይርበውም፤ ግራብ የተሰኘ ኩባንያ ሙሉ የምግብ ወጪውን ለመሸፈን ቃል ገብቷል።
ቅንጡ አፓርትመንትና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችም በተለያዩ ኩባንያዎች በስጦታ እንደሚቀርቡ የሀገሪቱ መንግስት አስታውቋል።
ሲንጋፖር
በፓሪስ የወርቅ ሜዳልያ ለሚያስገኙ አትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት (750 ሺህ ዶላር) እሰጣለሁ ያለችው ሲንጋፖር ለአትሌቶች ነጻ የአየር ትራንስፖርት ስጦታ አዘጋጅታለች።
በአቪየሽን ኢንዱስትሪው መሪ የሆነው የሲንጋፖር አየርመንገድ ሜዳልያ ለሚያስገኙ አትሌቶችና ለቤተሰቦቻቸው ለአንድ አመት የትኬት ወጪ እንደሚሸፍን ገልጿል።
ሆንግ ኮንግ
በፓሪስ ኦሎምፒክ 35 አትሌቶችን የምታሳትፈው ሆንግ ኮንግ ሜዳልያ ለሚያገኙት ሁሉም አትሌቶች የህይወት ዘመን የነጻ የባቡር ትራንስፖርት ትኬት እሸልማለሁ ብላለች።
የወርቅ ሜዳልያ ለሚያገኙ አትሌቶች 770 ሺህ ዶላር ሽልማት ለመስጠት ቃል የገባ ኩባንያ መኖሩም ተዘግቧል።