ለሚስቱ በተኮሰው ጥይት ልጁን ያጣው አባት ራሱን ለማጥፋት ሙከራ አድርጎ በጽኑ ሀሙማን ማቆያ ውስጥ ይገኛል
የ 8 አመቱ የሚኒሶታ ነዋሪ አሚር ሀርደን በቤተሰቦቹ መካከል በተፈጠረ ግጭት እናቱን ከአባቱ ጥቃት ለመከላከል ሲሞክር በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ አልፏል፡፡
እናቱ በተደጋጋሚ በአባቱ አካላዊ ጥቃት ሲደርስባት የሚመለከተው አሚር አደጋው በተፈጠረበት ቀን እናቱን ለመከላከል ከአባቱ እጅ ሽጉጥ ለመንጠቅ ሲሞክር ጭንቅላቱ እና አንገቱ ላይ በተተኮሰ ጥይት ነው ህይወቱ ያለፈው፡፡
ወላጅ አባቱ ዳንየር ሀርደን ሁኔታው ከተፈጠረ በኋላ እራሱን ለማጥፋት ሙከራ ቢያደርግም ሊተርፍ ችሏል፡፡
የአደጋ ጊዜ ጥሪ የተደረገለት ፖሊስ በስፍራው ሲደርስ አባት እና ልጅ በደም ተነክረው በተለያየ ቦታ ወድቀው ያገኛቸው ሲሆን ታዳጊው አሚር ሃርደን ወድያው ህይወቱ ሲያልፍ አባቱ ደግሞ በአስጊ ሁኔታ በጽኑ ህሙማን ማቆያ ውስጥ ይገኛል ነው የተባለው፡፡
አደጋውን በመመርመር ላይ የሚገኘው ፖሊስ ጉዳዩን ለፍርድ ቤት አቅርቧል፤ ፍርድ ቤትም አደጋውን ያደረሰው ሀርደን በሌለበት የፍርድ ሂደቱ እንዲቀጥል ወስኗል፡፡
በልጇ መስዋዕትነት በህይወት መትረፍ የቻለችው ቼሪሽ ኤድዋርድ ባለቤቷ በልጆቿ ፊት በተደጋጋሚ አካላዊ ጥቃት ይፈጽምባት እንደነበር በመጨረሻም የውድ ልጇን ህይወት እንዳስከፈላት ነው በጸጸት ውስጥ ሆና ለፖሊስ ቃሏን የሰጠችው፡፡
""እኔን ለማትረፍ የ8 አመት ህጻን ከ30 አመት ግዙፍ ሰው እጅ ሽጉጥ ለማስጣል ግብግብ መግጠሙ ልጄ ከልቤ መቼም እንዳይወጣ ያደረገ አጋጣሚ ነው፤ አባቱ እኔን መደብደብ ሲጀምር ወደ ጎረቤቶች ቤት እንዲሄድ እና እርዳታ እንዲጠራ ብጠይቀውም አኔን ከጥቃት ለመከላከል የመጨረሻውን መስዕዋትነት ከፍሏል" ስትልም ተናግራለች።
በቅርቡ ለ10 አመት የቆየ ትዳራቸው በዚህ ሁኔታ መቀጠል እንደማይችል እና መለያየት እንደምትፈልግ ለባለቤቷ ሀርድን ስትነግረው አንገቷን አንቆ ሊገድላት ሲል በተመሳሳይ ሟቹ ልጇ መካከል ገብቶ እንዳተረፋትም ቺሪሽ ገልጻለች፡፡
በወቅቱ በቤት ውስጥ ጥቃት ክስ ከፍታበት በፍርድ ሂደት ላይ እያለ የአሁኑ አጋጣሚ መፈጠሩን መግለጿንም ዴይሊ ሜል አስነብቧል።
ራሱን ለማጥፋት ባደረገው ሙከራ በድንገተኛ ክፍል በአስጊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝው የ30 አመቱ ሀርደን በህይወት የሚተርፍ ከሆነ በቀረበበት ክስ የእስር ቅጣት ይጠብቀዋል፡፡