በጭንቅላት ካንሰር ምክንያት በየአመቱ 200 ሺህ ሰዎች ህይወታቸው ያልፋል
ተመራማሪዎች የጭንቅላት ካንሰርን ጣት ላይ በሚወሰድ ናሙና መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂን ይፋ አድርገዋል።
ቴክኖሎጂው የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመለየት ጥቅም ላይ ከዋለው ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል።
የእንግሊዙ ኖቲንግሃም ትሬንት ዩኒቨርሲቲ ያስተዋወቀው ቴክኖሎጂ ሰዎች በቤታቸው ውስጥ ለጭንቅላት ካንሰር መጋለጣቸውን መለየት የሚያስችል ነው።
ጭንቅላይ ላይ የሚወጡ እጢዎች ሳይስፋፉ ከተደረሰባቸው በተለያዩ ህክምናዎች ስርጭቱን መግታት ይቻላል የሚሉት ተመራማሪዎች፥ እጢዎቹ ባልተጠበቀ ፍጥነት የማደግና የመሰራጨት እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
በቤት ውስጥ በቀላል ዘዴ ምርመራ ማድረግ መቻሉም ስርጭቱን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝ ያምናሉ።
በኤምአርአይ እና ሲቲ ስካን በሽታውን ለመለየት የሚጠፋ ጊዜንም ይቀንሳል ብለዋል።
የጭንቅላት እጢዎች እድገት ባልተጠበቀ ፍጥነት ሊጨምርና ህይወትን አደጋ ላይ ስለሚጥልም ከእጅ ላይ ናሙና በቀላሉ የሚወሰደው ናሙና በየቀኑ ክትትል ለማድረግ ሁነኛ መንገድ መሆኑን ነው የሚያክሉት።
በጭንቅላት ካንሰር በየአመቱ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት እንደመቀጠፉም ቴክኖሎጂው የሺዎችን ህይወት ለመታደግ እንደሚያግዝ ታምኖበታል።
የጭንቅላት እጢዎች በፍጥነት አንዳንዴም በዝግታ እንደሚያድጉ የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የካንሰር ህዋሳት ቁጥራቸው ጨምሮ መጠናቸውም ከፍ ሲል ወደ ጤነኛው ህዋስ ተዛምተው ጭንቅላት ውስጥ እብጠት ይፈጥራሉ።
በጭንቅላት ውስጥ የሚታዩ የካንሰር ህዋሳት በድጋሚ እንዳከሰቱ በቀዶ ህክምና እና ኬሞቴራፒ (የጨረር ህክምና) ይወገዳሉ።
የሰውነት መንቀጥቀጥ፣ የእይታ መደብዘዝ እና የሰውነት መስነፍ የጭንቅላት ካንሰር ምልክት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።