በሰው አእምሮ ውስጥ የሚቀበሩ ቺፕሶች ወደፊት የእጅ ስልኮችን ይተካሉ- መስክ
የመስክ የባዮቴክ ኩባንያ የ30 አመት እድሜ ባለው ግለሰብ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ቺፕስ የገጠመው ባለው ጥር ወር ነበር
ኤፍዲኤ ሁለተኛው የቺፕስ መቅበር ሙከራ እንዲደረግ ፍቃድ መስጠቱ ተገልጿል
በሰው አእምሮ ውስጥ የሚቀበሩ ቺፕሶች ወደፊት የእጅ ስልኮችን ሊተኩ አንደሚችሉ ኢሎን መስክ ገለጸ።
የአሜሪካዊው ቢሊየነር ኢሎን መስክ የሆነው የባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ኒውራሊንክ ባለፈው ጥር ወር የመጀመሪያውን ችፕስ በሰው አእምሮ ውስጥ የቀበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ሙኩራ እየተዘጋጀ ነው።
ወደፊት የእጅ ስልኮች በአእምሮ ውስጥ በቀጥታ በሚቀበሩ ቺፕሶች ስለሚተኩ ከጥቅም ውጭ ይሆናሉ ሲል ቢሊየነሩ ኢሎን መስክ ግምት ማስቀመጡን አርቲ ዘግቧል። የመስክ የባዮቴክ ኩባንያ የ30 አመት እድሜ ባለው ግለሰብ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ችፕስ የገጠመው ባለው ጥር ወር ነበር።
የሳንቲም መጠን ያላትን ቺፕስ የሰው ልጅን እንቅስቃሴ ፍላጎት ከሚያዘው የአእምሮ ክፍል ላይ በቀዶ ጥገና እንድትቀመጥ ተደርጓል። ይህቺ ቺፕስ "የአእምሮን እንቅስቃሴ በመመዝገብ እና የእንቅስቃሴ ፍላጎትን ወደሚተረጉም መተግበሪያ ወይም አፕ" ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ ውላለች።
መስክ ይህን የቅርብ ትንበያውን ያጋራው "ኖት ኢሎን መስክ" ለተባለ የአሽሙር የኤክስ አካውንት ፓስት በሰጠው ምላሽ ነው።
ዋናው መልእክት "ስልካችሁን በማሰብ ብቻ ለመቆጣጠር ኒውራሊንክ ኢንተርፌስ መጫን ትፈልጋላችሁ" የሚል ነበር ፓስቱ።
በዚህ መልእክት ስር ኢሎን መስክ "ወደ ፊት ስልክ አይኖርም፤ የሚኖሩት ኒውራሊንኮች ናቸው" ሲል መልሷል።
ኒውራሊንክ ባለፈው አመት በሰጠው መግለጫ ፕሪሳይዝ ሮቦቲካሊ ኢምፕላንትልድ ብሬን ኮምፒውተር(ፒአርአይኤሜኢ) ፕሮግራም አላማ ሙሉ በሙሉ የሚቀበር እና ዋየርለስ ብሬን ኮምፒውተር በማልማት ሰዎች በማሰብ ብቻ የኮምፒውተር ከርሰር ወይም ኪቦርድ እንዲቆጣጠሩ ማስቻል እንደሆነ ገልጾ ነበር።
ይህ አይነስውራንን፣ ሰውነታቸው የማይታዘዝላቸውን እና የመሳሰሉ የአካል ጉዳት ያለባቸውን እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የአእምሮ ውስንነት፣ ድብርት እና ስኪዞፈርኒያ አይነት በሽታዎች ያሉባቸውን ሰዎች ለማከም መንገድ የሚጠርግ ነው ተብሏል።
መስክ በፈረንጆች 2018 ከጆይ ሮጋን ባደረገው ቃለ ምልልስ ኒውራሊንክ ሰዎች ቃላት ሳያወጡ እንዲግባቡ ወይም ሀሳብ እንዲለዋወጡ ሊያስችላቸው ይችላል ብሏል።
የአሜሪካ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር(ኤፍዳኤ) የመጀመሪያው የቺፕስ ቀበራ ወይም ቸፕስ ኢምላንቴሽን ያጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር ነበር።
ባለፈው ጥር ወር የቺፕስ ቀበራው ከተካሄደ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ የተቀበረለት ሰው "ሙሉ በሙሉ ማገገሙን እና ምንም ህመም እንደሌለበት" እንዲሁም የኮምፒውተር ማውዝን "በማሰብ ብቻ" በስክሪን ላይ ማንቀሳቀስ መቻሉን መስክ ሪፖርት ማድረጉ ይታወሳል።
ነገርግን ባለፈው ግንቦት ወር በበአእምሮ ውስጥ የተቀበረች ትንሽ ሾቦ ከቦታዋ በመንሸራተቷ ምክንያት ትንሽ ችግር አጋጥሞት እንደነበር አምኗል።
ያም ሆኖ ኤፍዲኤ ሁለተኛው የቺፕስ መቅበር ሙከራ እንዲደረግ ፍቃድ መስጠቱን ዋል ስትሬት ባለፈው ወር ዘግቧል።
በዚህ ወር ይካሄዳል በተባለው ሁለተኛው ሙከራ፣ ቺፕሱ እንዳይንሸራተት ጠለቅ ብሎ ወደ አእምሮ ውስጥ እንዲቀበር ይደረጋል ተብሏል።ያም ሆኖ ኤፍዲኤ ሁለተኛው የቺፕስ መቅበር ሙከራ እንዲደረግ ፍቃድ መስጠቱን ዋል ስትሬት ባለፈው ወር ዘግቧል።