በማሰብ ብቻ ኮምፒውተርና ስልኮችን ማዘዝ የሚያስችለው ቺፕ - "ቴሌፓቲ"
የኤለን መስክ ኩባንያ ኒውራሊንክ ገመድ አልባ ቺፑን ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ መቅበር መጀመሩን አስታውቋል
ቺፑ ሰውነታቸው የማይታዘዝላቸውና አይነ ስውራን ኮምፒውተር እና ስልክ በቀላሉ እንዲጠቀሙ ያግዛል ተብሏል
የአለማችን ቁጥር አንድ ቱጃር ኤለን መስክ ኩባንያ ኒውራሊንክ ገመድ አልባ ቺፕ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ መግጠሙን አስታወቀ።
ቺፑ የተገጠመለት የነርቭ ችግር ያለበት ግለሰብ ከህመሙ ማገገም መጀመሩንም ነው ኩባንያው የገለጸው።
ኒውራሊንክ ኩባንያ ያመረተው ገመድ አልባ ቺፕ ዋነኛ ተግባር የሰው ልጅ አዕምሮን ከኮምፒውተር ጋር ማገናኘት ነው።
ኩባንያው ቺፑን በሰው ልጅ አዕምሮ ላይ እንዲቀብር በአሜሪካ የምግብና መድሃኒት አስተዳደር ባለስልጣን በግንቦት ወር ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፥ ሙከራው ሰውነታቸው ለማይታዘዛቸው(ፓራላይዝ) እና ዐይነ ስውራን ትልቅ ብስራት ነው ተብሏል።
የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች ኮምፒውተር እና ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በቀላሉ እንዲጠቀሙ ይረዳል የተባለው ቺፕ፥ የአዕምሮን የእንቅስቃሴ ሃሳብ በ64 ከጸጉር የቀጠኑ ገመዶች እየተከታተለ ለኮምፒውተር በብሉቱዝ መረጃ ይልካል።
ቺፑ የተገጠመላቸው ሰዎች ሊያደርጉት ያሰቡትን ነገርም የሮቦት ቴክኖሎጂው ወዲያውኑ አንብቦ ለኮምፒውተሩ መረጃ ስለሚሰጥ በቅጽበት የፈቀዱት ይፈጸማል ተብሏል።
ኒውራሊንክ ለስድስት አመት የተመራመረበት ገመድ አልባ ቺፕ “ቴሌፓቲ” እንደሚሰኝ የቴክኖሎጂ ኩባንያው ባለቤት ኤለን መስክ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ቴሌፓቲ “ስልክም ሆነ ኮምፒውተራችን በአዕምሯችን በማሰብ ብቻ መቆጣጠር ያስችላል” ያሉት መስክ፥ የመጀመሪያዎቹ የቺፑ ተጠቃሚዎች እጃቸውን ያጡና ማዘዝ የማይችሉ ሰዎች ይሆናሉ ብለዋል።
መስክ ይህ ቴክኖሎጂ ለቀድሞው ብሪታንያዊ ተመራማሪ ስቴፈን ሃውኪንግ ቢደርስ ሊፈጥረው የሚችለውን ተዐምር መገመት አይከብድም ባይ ናቸው።
በሰው ልጅ አዕምሮ ውስጥ ቺፕ መግጠም በመጀመር የኤለን መስኩ ኒውራሊንክ የመጀምሪያው አይደለም።
የአሜሪካው ብላክሮክ ኒውሮቴክ በፈረንጆቹ 2004 ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የሰው ልጅ አዕምሮን ከኮምፒውተር ጋር የሚያገናኝ መሳሪያ መግጠም የጀመረው።
በአሜሪካ የተደረጉ ሁለት ጥናቶች በአዕምሮ ውስጥ የሚቀበሩ ጥቃቅን ቺፖች መንቀሳቀስ ለማይችሉ (ፓራላይዝ) ሰዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማሳየታቸውን አመላክተዋል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
የስዊትዘርላንድ አጥኚዎችም ባለፈው አመት አዕምሮ ላይ በተሳካ ሁኔታ ኮምፒውተር መቅበራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
በዚህም ሰውነቱ የማይታዘዝለት አንድ የኔዘርላንድስ ዜጋ ጭንቅላቱ ውስጥ በተቀበረለት ቴክኖሎጂ አማካይነት ስለመራመድ በማሰብ ብቻ መራመድ መቻሉ መነገሩ አይዘነጋም።