አሜሪካ ማይክሮ ቺፕስ ቴክኖሎጂ በሰዎች አካል ውስጥ እንዲገጠም ፈቀደች
በኢለን መስክ የተቋቋመው ኒውራሊንክ ኩባንያ በሰዎች አካል ውስጥ ቺፕስ የማስገባት ሙከራ እንዲጀምር ፈቃድ አግኝቷል
ኩባንያው በቅርቡ ቴክኖሎጂውን በበጎ ፈቃደኞች ላይ እንደሚሞክር ተገልጿል
አሜሪካ የሰው ልጅ አዕምሮን ከኮምፒውተር ጋር የሚያገናኝ ቴክኖሎጂ በሰዎች ላይ እንዲገጠም ፈቀደች፡፡
አሜሪካዊው ታዋቂ ባለጸጋ ኢለን መስክ ኒውራሊንክ የተሰኘ ኩባንያን በፈረንጆቹ 2016 ላይ ነበር የመሰረተው፡፡
ይህ ኩባንያ ዋነኛ ዓላማውም የሰዎችን አዕምሮ የመስራት አቅም ለማሳደግ በሰውነት ውስጥ ማይክሮ ቺፕስ መግጠም ዋነኛ አላማው ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ኩባንያው በ2020 ላይ ወደ ስራ የመግባት እቅድ ቢኖረውም በውጤታማነቱ ላይ ጥርጣሬ የገባቸው ባለሙያዎች እና ከተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት እና ባለሙያዎች ተቃውሞ ገጥሞት ቆይቷል ተብሏል፡፡
ኒውራሊንክ ኩባንያ ማይክሮ ቺፕስ በዝንጆሮዎች ላይ ሲሞክር መቆየቱን ገልጾ የአዕምሮ ውጤታማነትን ማሳደጉ ተረጋግጧል ብሏል፡፡
ኩባንያው ከዚህ በፊት ቴክኖሎጂውን በሰዎች ላይ እንዲተገብር ፈቃድ እንዲሰጠው ለአሜሪካ ምግብ እና መድሃኒት አስተዳድርን ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ጥያቄው ውድቅ ተደርጎበት ነበር፡፡
ተቋሙ አሁን ላይ የሰውችን የአዕምሮ ውጤታማነት ለማሳደግ ቴክኖሎጂውን በሰዎች ላይ መተግበር እንደሚችል ፈቃድ መስጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ኒውራሊንክ ኩባንያ ባወጣው መግለጫ ከአሜሪካ ምግብ እና መድሃኒት አስተዳድር ፈቃድ ማግኘቱን ገልጾ በቅርቡ ቴክኖሎጂውን በበጎ ፈቃደኞች ላይ መተግበር እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ይተገበራል የተባለው ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በሰው አካል ላይ ማይክሮ ቺፕስ በማስገባት ሰዎች ስራዎችን ሲያከናውኑ አዕምሯቸው እንዳይለግም አወንታዊ መልዕክት ወደ አዕምሮ እንዲላክ እና ስራው አልያም ውሳኔው እንዲፈጸም የሚያደርግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ቴክኖሎጂው በመጀመሪያ አልታዘዝ ያሉ የሰውነት ክፍሎች እንዲንቀሳቀሱ ፣ማየት ባልቻሉ ሰዎች ላይ እይታን እንዲጎናጸፉ እና ሌሎችንም ተግባራት ውጤታማ ማድረግ ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
ቀስ በቀስ ደግሞ በሌሎች የጠሟላ አካል ባላቸው እና የቴክኖሎጂ አገልግሎቱን በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ይተገበራልም ተብሏል፡፡
የኒውራሊንክ ኩባንያ መስራች ኢለን መስክ ከዚህ በፊት ስለ ድርጅታቸው እንዳሉት የሰው ልጆች በአርቲፊሺያል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂዎች የመዋጥ አደጋ እንደተደቀነባቸው እና ኒውራሊንክ እና መሰል ኩባንያዎች ከዚህ አደጋ የማዳን አቅም አላቸው ብለው ነበር፡፡
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በበኩላቸው የኒውራሊንክ ቴክኖሎጂ በብዙሃኑ ሰዎች ላይ ከመተግበሩ በፊት ተጨማሪ የጥንቃቄ ጥናቶች እና እርምጃዎች እንዲደረጉ አሳስበዋል፡፡
የስዊዘርላንድ ተመራማሪዎች ከሰሞኑ የሰው ልጅን አዕምሮ ከኮምፒውተር ጋር በማገናኘት መንቀሳቀስ ያልቻለ ሰውን ለአዕምሮው ትችላለህ የሚል መልዕክት እንዲደርሰው በማድረግ እንዲራመድ ማድረግ ችለዋል፡፡