በአሜሪካ ማይክሮ ቺፕስ ቴክኖሎጂ በሰዎች አካል ውስጥ መግጠም በቅርቡ ይጀመራል ተባለ
በኢለን መስክ የተቋቋመው ኒውራሊንክ ኩባንያ በሰዎች አካል ውስጥ ቺፕስ የማስገባት ሙከራ እንዲጀምር ፈቃድ ማግኘቱ ይታወሳል
የህክምና አገልግሎቱን ለማግኘት ከ22 ዓመት በላይ እና መራመድ ያልቻሉ አካል ጉዳተኛ መሆን ይጠበቅባቸዋል
በአሜሪካ ማይክሮ ቺፕስ ቴክኖሎጂ በሰዎች አካል ውስጥ መግጠም በቅርቡ ይጀመራል ተባለ።
ንብረትነቱ የአሜሪካዊው ታዋቂ የዓለማችን ባለጸጋ በሆኑት ኢለን መስክ የሆነው ኒውራሊንክ የተሰኘው ኩባንያ በፈረንጆቹ 2016 ላይ ነበር የመሰረተው፡፡
ይህ ኩባንያ ዋነኛ ዓላማውም በተለያዩ ምክንያቶች እንደልብ መስራት ያልቻሉ የሰዎችን አዕምሮ አቅም ማሳደግ እንደሆነ ተገልጻል።
የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም በሰውነት ውስጥ ማይክሮ ቺፕስ በመግጠም የአካል ጉዳት ያጋጠማቸው ሰዎችን መርዳት ዋነኛ አላማው ማድረጉ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡
ኩባንያው በ2020 ላይ ወደ ስራ የመግባት እቅድ ቢኖረውም በውጤታማነቱ ላይ ጥርጣሬ በገባቸው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት እና ባለሙያዎች ተቃውሞ ገጥሞት ቆይቷል፡፡
ኒውራሊንክ ኩባንያ ማይክሮ ቺፕስ በዝንጆሮዎች እና አሳማዎች ላይ ሲሞክር መቆየቱን ገልጾ የአዕምሮ ውጤታማነትን ማሳደጉ ተረጋግጧል ብሏል፡፡
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ኩባንያው ከዚህ በፊት ቴክኖሎጂውን በሰዎች ላይ እንዲተገብር ፈቃድ እንዲሰጠው ለአሜሪካ ምግብ እና መድሃኒት አስተዳድርን ጠይቆ ውድቅ ከደርገበት በኋላ ከአራት ወር በፊት በሰዎች ላይ እንዲሞከር ፈቃድ ተሰጥቶታል።
የኒውራሊንክ ኩባንያ ባለቤት ኢለን መስክ በኤክስ ወይም በቀድሞ ስሙ ትዊተር ገጻቸው እንዳሉት የሰዎችን አዕምሮ ለማገዝ የተቋቋመው ኒውራሊንክ ችፕስን በበጎ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ መግጠሙ በቅርቡ ይጀመራል ብለዋል።
መስክ አክለውም ሙከራው በሰው ልጆች ላይ እንዲጀመር ከአሜሪካ ምግብ እና መድሃኒት አስተዳድር ፈቃድ ሰጥቷል ኩባንያውም ቅድመ ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ገልጸዋል።
ይተገበራል የተባለው ይህ አዲስ ቴክኖሎጂ በሰው አካል ላይ ማይክሮ ቺፕስ በማስገባት ሰዎች ስራዎችን ሲያከናውኑ አዕምሯቸው እንዳይለግም አወንታዊ መልዕክት ወደ አዕምሮ እንዲላክ እና ስራው አልያም ውሳኔው እንዲፈጸም የሚያደርግ ነው።
ቴክኖሎጂው በመጀመሪያ አልታዘዝ ያሉ የሰውነት ክፍሎች እንዲንቀሳቀሱ ፣ማየት ባልቻሉ ሰዎች ላይ እይታን እንዲጎናጸፉ እና ሌሎችንም ተግባራት ውጤታማ ማድረግ ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
ቀስ በቀስ ደግሞ በሌሎች የተሟላ አካል ባላቸው እና የቴክኖሎጂ አገልግሎቱን በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ይተገበራልም ተብሏል፡፡
ይህን የኒውራሊንክ አገልግሎት ለማግኘት 22 ዓመት እና ከዛ በላይ ለሆኑ አካል ጉዳተኛ ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ተገልጿል።
የኒውራሊንክ ኩባንያ መስራች ኢለን መስክ ከዚህ በፊት ስለ ድርጅታቸው እንዳሉት የሰው ልጆች በአርቲፊሺያል ኢንተሊጀንስ ቴክኖሎጂዎች የመዋጥ አደጋ እንደተደቀነባቸው እና ኒውራሊንክ እና መሰል ኩባንያዎች ከዚህ አደጋ የማዳን አቅም አላቸው ብለው ነበር፡፡
የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በበኩላቸው የኒውራሊንክ ቴክኖሎጂ በብዙሃኑ ሰዎች ላይ ከመተግበሩ በፊት ተጨማሪ የጥንቃቄ ጥናቶች እና እርምጃዎች እንዲደረጉ አሳስበዋል፡፡