ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው እንዲታገድ የወሰኑበትን ቲክቶክ ተቀላቀሉ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አዲስ በከፈቱት የቲክቶክ አካውንት በስአታት ውስጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተከታይ አግኝተዋል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም በየካቲት ወር የቲክቶክ አካውንት መክፈታቸው ይታወሳል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክን ተቀላቀሉ።
ትራምፕ ትናንት ምሽት የቻይናውን ባይትዳንስ ኩባንያ የቪዲዮ ማጋሪያ መቀላቀላቸውን የሚያበስር ቪዲዮ በአዲሱ አካውንታቸው ለቀዋል።
ቪዲዮውን ከ30 ሚሊየን በላይ ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን፥ አዲሱ አካውንት በስአታት ውስጥ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ተከታይ ማፍራት ችሏል።
በህዳር ወር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው የሚፎካከሩት ትራምፕ ቲክቶክን መቀላቀላቸው ወጣት መራጮችን ለማግኘት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል።
የቅስቀሳ ቡድናቸው ቃል አቀባይ ስቲቭ ቹንግም በአዲሱ የትራምፕ የቲክቶክ አካውንት የተለቀቀው ቪዲዮ ተደራሽነት “በሁሉም ግንባሮች አሸናፊነታችን ያሳየ ነው” ብለዋል።
በኤክስ (ትዊተር) ከ87 ሚሊየን በላይ፤ በራሳቸው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ትሩዝ ሶሻል ደግሞ ከ7 ሚሊየን በላይ ተከታይ ያላቸው ዶናልድ ትራምፕ ቲክቶክን መቀላቀላቸው የማህበራዊ ትስስር ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውን እንደሚያሳድግላቸው ሬውተርስ ዘግቧል።
በ2020 ፕሬዝዳንት እያሉ ቲክቶክን ለማገድ ያደረጉት ሙከራ በፍርድቤት የታገደባቸው የ77 አመቱ ትራምፕ፥ ባለፈው መጋቢት ወርም የአጭር ቪዲዮ ማጋሪያው የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ቲክቶክን ማገድ ሜታን ከማጠናከር ውጭ ፋይዳ የለውም፤ ወጣት አሜሪካውያንንም ይጎዳል የሚል አስተያየታቸውም ሲያወዛግብ ቆይቷል።
@realdonaldtrump Launching my TikTok at @UFC ♬ original sound - President Donald J Trump
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም የቻይናው ባይትዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው ቲክቶክ የአሜሪካውያንን መረጃ ለቤጂንግ ያቀብላል በሚል የትራምፕን የቀድሞ ክስ ሲያጠናክሩ መቆየታቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ በአሜሪካ ከ170 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቲክቶክ እንዲታገድ የሚያደርግ ህግ ላይ ፊርማቸውን ማሳረፋቸውም አይዘነጋም።
የትራምፕ ተፎካካሪ ጆ ባይደን ከውሳኔው አስቀድመው ቲክቶክን ተቀላቅለው የምርጫ ቅስቀሳ ቪዲዮዎችን ማጋራት ከጀመሩ ግን አራት ወራት ተቆጥረዋል።
የ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተፎካካሪዎቹ ቲክቶክ ላይ ስጋታቸው አሁንም እንዳለ ቢሆንም ወጣት መራጮችን ለማግኘት መተግበሪያውን ዋነኛ መሳሪያ አድርገው ለመጠቀም ወስነዋል።
እስከ ቀጣዩ ግንቦት ወር ድርሻውን ለአሜሪካውያን እንዲሸጥ የተወሰነበት የቲክቶክ ባለቤት ኩባንያ ባይትዳንስ ግን የአሜሪካውያንን መረጃ ለቤጂንግ አሳልፎ እንደማይሰጥ በመጥቀስ የፍርድቤት ክርክሩ እንደሚቀጥል አስታውቋል።