ቲክቶክን በአሜሪካ ማገድ የ170 ሚሊየን ሰዎችን የመናገር ነፃነት መርገጥ መሆኑን ኩባንያው አስታወቀ
የአሜሪካ ምክር ቤት ቲክቶክን ለማገድ የሚያስችል ውሳኔ አጽድቋል
አሜሪካ የቲክቶክ ባለቤት ባይቴዳንስ ለቤጂንግ መንግስት ታዛዥ ነው በማለት ክስ ታቀርባለች
ቲክቶክ በአሜሪካ ውስጥ በመተግበሪያው ላይ የሚጣል ማንኛውም እግድ የ170 ሚሊዮን የሀገሪቱን ዜጎች “የመናገር ነፃነትን ይረግጣል” አለ
የአሜሪካ የህዝብ የተወካዮች ምክር ቤት የመተግበሪያው ባለቤት ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ካላቋረጠ ቲክቶክን ሊያግድ የሚያስችል ውሳኔ ላይ ድምጽ ሰጥቷል።
የአሜሪካ ባለስልጣንት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቲክቶክ በወጣቶች ዘንድ ተወዳጅነቱ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ በእጅጉ እንደሚያሳችባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
አሜሪካ የቲክቶክ ባለቤት ባይቴዳንስ ለቤጂንግ መንግስት ታዛዥ ነው በማለት ክስ የምታቀርብ ሲሆን፤ ኩባያው በተደጋጋሚ የሚቀርቡበትን ውንጀላዎች ውድቅ ሲያደርግ ቆይቷል።
የአሜሪካ ሴኔት ቲክቶክን ለማገድ የተዘጋጀው ውሳኔ ላይ በቀጣይ ሳምንት ድምጽ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዚህ ቀደም ህጉን ፈርመው እንደሚያጸደቁ መግለጻቸው ይታወሳል።
ውሳኔው ህግ ሆኖ ከወጣ ባይተንዳነስ ኩባንያ የቲክቶክ ድርሻ ለመሸጥ 9 ወራት ብቻ የሚኖረው ሲሆን፤ ካለሆነ ግን በአሜሪካ እንዳይሰራ ሊታገድ ይችላል ነው የተባለው።
የቲክቶክ ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፤ ውሳኔው የ170 ሚሊየን አሜሪካውያንን የመናገር ነጻነት የሚረግጥ ነው ብሏል።
እንዲሁም ቲክቶክን ማገድ በአሜሪካ ያሉ 7 ሚሊየን ንግዶችን እንደሚጎዳ እና የአሜሪካን ኢኮኖሚም በዓመት 24 ቢሊየን ዶላር እንደሚያሳጣም ቲክቶክ አስታውቋል።
ቲክቶክ አክሎም “ባይተንዳንስ የቻናም ይሆን የየትኛውም ሀገር ወኪልና ተላላኪ አይደለም” ያለ ሲሆን፤ ባይትዳንስ 60 በመቶው አክሲዮን በዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ 20 በመቶው በሰራተኞች እና 20 በመቶው በመስራቾቹ የተያዘ መሆኑን ገልጿል።
እንዲሁም ከአምቶ የቦርድ አባላት ውስጥ ሶስቱ አሜሪካውያን መሆናቸውንም ኩባንያው አስታውቋል።
በፈረንጆቹ 2016 ላይ በቻይና የተሰራው ቲክቶክ የማህበራዊ ትስስር ገጽ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በቢሊየን የሚቆጠሩ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል።
ይህ መተግበሪያ አጫጭር ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በአጭር ጊዜ ለብዙዎች እንዲደርስ ማድረግ የሚያስችል ሲሆን ለብዙዎችም የገቢ ምንጭ ሆኗል።
ይህ ፈጣን መተግበሪያ በቻይና መሰራቱን ተከትሎ ምዕራባዊያን ሀገራት በጥርጣሬ የሚያዩት ሲሆን በተለይም አሜሪካ በዚህ መተግበሪያ ላይ እምነት እንደሌላት ስትናገር ቆይታለች።