የአጫጭር ቪዲዮ መተግበሪያዎቹ እንደ ክፍያ ስርዓታቸው ከ50 እስከ 10 ሺህ ዶላር የሚከፍሉ ናቸው
አሜሪካ ከሰሞኑ ቲክቶክን በቀጣይ ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለማገድ የሚያስችል ህግ ማጽደቋን ተከትሎ በርካቶች ስጋት ውስጥ ገብተዋል።
አሜሪካ ባጸደቀችው አዲሱ ህግ ቲክቶክ በቀጣይ 9 ወራት ውስጥ ለአሜሪካ ኩባንያዎች የማይሸጥ ከሆነ መተግበሪያውን ሙሉ በሙሉ እንደምታግድ የሚገልጽ ሲሆን፤ የቲክቶክ ባለቤት የሆነው የቻይናው ባይተንደንስ ግን ቲክቶክን የመሸጥ እቅድ የለኝም ብሏል።
የአሜሪካ እና የቲክቶክ ኩባንያን እሰጣ ገባ ተከትሎም በሚሊየን የሚቆጠሩ ቲክቶከሮች እና ተጠቃሚዎች እንደተባለው ቲክቶክ ከታገደ “ያለን አማራጭ ምንድን ነው?” የሚሉ ጥያቄዎችን እያነሱ ነው።
ይህንን ለመመለስ፣ አምስት የቲክቶክ አማራጭ የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያዎችን ዝርዝር እንደሚከተለው አዘጋጅተናል፤
1. ኢንስታግራም ሪልስ
ሜታ ኩባያ በፌስቡክ፣ ዋትስአፕ እና ኢንስታግራም በመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎቹ በዓለም ላይ ትልቁን ድርሻ መቆጣጠሩ ይታወቃል። ሆኖም ግን ቲክቶክ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎም ሜታ ኩባንያ በኢንስታግረም ላይ “ሪልስ” የተሰኘ የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ አማራጭን እንዲያካትት አድርጎታል።
ወደፊት ቲክቶክ በአሜሪካ የሚታገድ ከሆነ “ኢንስታግራም ሪልስ” ከቀዳሚዎች አማራጮች ውስጥ እንዱ እንደሚሆን ይጠበቃል። ሪልስ ከቲክቶክ ጋር ተመሳሳይ ገጽ ያለው ሲሆን፤ አዝኛኝ ቪዲዮዎች የሚጋሩበት መሆኑም አማራጭ ያደርገዋል።
ገቢ ከማስገኘት አንጻም ኢንስታግራም በቅርቡ ገንዘብ መስራት የሚያስችል አገልግሎት ማስታዋወቁ ይታወሳል።
በዚህም መስረት ኢንስታግራም አንድ ሚሊየን እና ከዚያ በላይ እይታ ላገኙ ቪዲዮዎች በሚያገኙት ኢንጌጅመንት ላይ በመመርኮዝ ከ500 እስከ 10 ሺህ ዶላር ድረስ ይከፍላል ተብሏል።
2. ዩትዩብ ሾርት
ዩ ትዩብ ከቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያዎች ውስጥ የሁሉም አእምሮ ላይ ቀድሞ የሚመጣ እና ጤናማ የሆነ የኦንላይን ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስበት ነው።
ሆኖም ግን ቲክቶክ በድንገት በአጫጭር ቪዲዮዎች ገበያውን መስበሩን ተከትሎም ዩ ትዮብም “ዩትዩብ ሾርት” የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ አገልግሎት መጨመሩ አይዘነጋም ።
በበርካቶች ተመራጭ የሆነው ዩ ትዩብ ቲክቶክ የሚዘጋ ከሆነ አማራጭ ይሆናል ከተባሉት ውስጥ ከፍተኛውን ግምት አግኝቷል።
ዩትዩብ ሾርት ገንዘብ መስራትም የሚቻል ሲሆን፤ ሆኖም ግን የክፍያ ስርዓቱ ውስጥ ለመግባት ተጠቃሚዎች በ90 ቀናት ውስጥ 1 ሺህ ተከታዮች እና 10 ሚሊየን እይታ መግኘት የግድ ሊሟላ የሚገባ መስፍረት ነው። ዩትዩብ ሾርት በአንድ ሚሊየን እይታ ከ50 እስከ 70 የአሜሪካ ዶላር ይከፍላል።
3 ስናፕቻት ስፖትላይት
ስናፕቻት በታዳጊ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች ዘንድ በጣም ታዋቂው እና ተመራጭ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ እንደሆነ ይታወቃል፤ ወጣቶቹ የአጭር ቪዲዮዎች ይዘትም ዋነኛ ተጠቃሚዎች ናቸው።
ስናፕቻት ቲክቶክ ተወዳጅነትን እያተረፈ መምጣቱን ተከትሎ ቲክቶክን የሚገዳደር “ስፖትላይት” የተሰኘ አገልግሎት ማካተቱ የሚታወስ ሲሆን፤ የስፖትላይት ክፍል ተጠቃሚዎች ከሚወዷቸው የይዘት ፈጣሪዎች ጋር እንዲገናኙ የሚያችል ነው።
ስናፕቻት ስፖትላይት ገንዘብ መስራትም ያስችላል። ምንም እንኳ እንደ ሌሎቹ በሚሊየን እይታ ቋሚ የሆነ የክፍያ መጠን ባይኖረውም፤ በተመልካች ብዛትና እና ተሳትፎ መለኪያዎች ላይ በመመስረት በአንድ እይታ ከ0.01 እስከ 0.10 የአሜሪካ ዶላር መካከል ይከፍላል።
4. ላይኪ (Likee)
ከዋና ዋና የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች በመቀጠል ላይኪ በአጭር የቪዲዮ መተግበሪያ ላይ ዘርፍ ብቅ ያለ አዲስ ተፎካካሪ መተግበሪያ ነው።
ላይኪ (Likee) የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያ ከቲክቶክ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ገጽታ ያለው ሲሆን፤ በሙዚቃ ላይ የበለጠ ትኩረት ማደረጉ የተለየ ያደርገዋል።
በላይኪ በአጭር የቪዲዮ መተግበሪያ ገንዘብ መስራተ የሚቻል ሲሆን፤ ቪዲዮ የሚያጋሩ ተጠቃሚዎቹንም እንደየተከታዮቻቸው እና አንደሚያገኙት የእይታ ብዛት በሶስት ምድብ በመክፈል ክፍያ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
በዚህም መሰረት
ኬ1 ክራወንስ በተባለ ምድብ ያሉ የይዘት ፈጣሪዎች 400 ዶላር እና ከዚያ በላይ
ኬ2 ክራወንስ በተባለ ምድብ ያሉ የይዘት ፈጣሪዎች 200 ዶላርና ከዚያ በላይ
ኬ3 ክራወንስ በተባለ ምድብ ያሉ የይዘት ፈጣሪዎች 50 ዶላርና ከዚያ በላይ መስራት ይችላሉ
5. ትሪለር
ትሪለር የተባለው የአጫጭር ቪዲዮ መተግበሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ተጠቃሚዎችን እያፈራ ነው የተባለ ሲሆን፤ ምክንያቱ ደግሞ ታዋቂ ሰዎች መተግበሪያውን መጠቀም መጀመራቸው ነው ተብሏል
ትሪለር ከቲክቶክ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የገጽ እይታ ያለው ሲሆን፤ ከዚህም በላይ ግን እንደ ስፖርት፣ ኮሜዲኪ፣ ነጥበብ እና የመሳሰሉት ክፍሎች የተከፋፈለ መሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭ እያደረገው ነው ተብሏል
ገንዘብ ከመስራት አንጻር ትሪለር አሁን ላይ ምንም አይነት የክፍያ ስርዓት የለውም የተባለ ሲሆን፤ ሆኖም ግን ኩባንየው ተጠቃሚዎች ከቀጥታ ስርጭት (live stream) ገንዘብ መስራት የሚችሉበትን አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰሩ ነው ተብሏል።