ቲክቶክን ማን ሊገዛው ይችላል?
የዓለማችን ዋነኛ ሸማች የሚባሉት አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት የቻይናን ተጽዕኖ ለመቀነስ በሚል ቲክቶክን በማገድ ላይ ናቸው
አሜሪካ ቲክቶክ ካልተሸጠ በሀገሯ እና ወዳጆቿ እንዳይሰራ ለማገድ ቀነ ገደብ አስቀምጣለች
ቲክቶክን ማን ሊገዛው ይችላል?
በቀርብ ዓመታት ውስጥ በመላው ዓለም ተጽዕኖ መፍጠር የቻለው ቲክቶክ የተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጽ በበርካታ ሀገራት እገዳ እየገጠመው ይገኛል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቲክቶክ በአሜሪካ ላይ ደህንነት ደቅኗል በሚል ኩባንያው ካልተሸጠ እንዲታገድ የሚያስገድድ ህግ በፊርማቸው አጽድቀዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ቲክቶክ እንዲሸጥ አልያም እንዲታገድ የተላለፈውን ውሳኔ ተቃውሞ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው አስታውቋል፡፡
የተላለፈው ውሳኔ ተፈጻሚነት ቢኖረው በሚል ቲክቶክን ለመግዛት ፍላጎታቸውን ያሳዩ ሲኖሩ የተወሰኑት ደግሞ መሸጡ እንደማይቀር አምነው ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ ያሉ ኩባንያዎች እንዳሉ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ አሜሪካ ይህ ውሳኔ ማሳለፏን ተከትሎ የቲክቶክ ኩባንያ ዋጋ ከነበረበት 100 ቢሊዮን ዶላር ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል ተብሏል፡፡
የቀድሞው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ቲክቶክን ለመግዛት ጥያቄ አቀረቡ
ቲክቶክ በአሜሪካ የተላለፈበት ውሳኔ እንዳይፈጸም የጀመረው ጥረት ባይሳካ ለመሸጥ ይገደዳል የተባለ ሲሆን ኩባንያውን ለመግዛት ጥረት እያደረጉ ካሉ ድርጅቶች መካከል አብዛኞቹ መሰረታቸውን አሜሪካ ያደረጉ ናቸው፡፡
ከነዚህ መካከልም ማይክሮሶፍት፣ አማዞን፣ ኦራስል፣ቬራይዞን ፣ ኤቲኤንድ ቲ፣ ብሉምበርግ እና ሌሎችም ድርጅቶች በቡድን እና በተናጥል ለመግዛት በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ቻይና በበኩሏ ቲክቶክ የቤጂንግ መንግስት ድርሻ እንደሌለው የምዕራባዊያን ሀገራ እገዳ ለማስተላለፍ ምክንያታቸው ፖለቲካ እንጂ ሌላ አይደለም ብላለች፡፡
ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ 150 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት ሲሆን በመላው ዓለም ደግሞ ከ2 ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ሲኖሩት ዓመታዊ ገቢውም ከ120 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡
በኢትዮጵያዊያን ከተወደዱ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል ቲክቶክ አንዱ ሲሆን ወርሃዊ ንቁ የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡