የብራዚል ፖሊስ በማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች አንቶኒ ላይ ከፍቶት የነበረውን ምርመራ አቋረጠ
የዩናይትድ የክንፍ ተጫዋች አንቶኒ ከአመት በፊት በቤት ውስጥ ጥቃት በ3 ሴቶች ተከሶ ነበር
ፖሊስ ምርማራውን ቢያቋርጥም አቃቢ ህግ ጉዳዩ ድጋሚ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ውሳኔ ማሳለፉ ተሰምቷል
በማንችስተር ዩናይትድ የመስመር ተጫዋች አንቶኒ ላይ የበራዚል ፖሊስ ሲያደርገው የነበረውን ምርመራ ማቋረጡን አስታወቀ።
በ24 አመቱ ብራዚላዊ ላይ ባለፈው አመት መስከረም ወር ሶስት ሴቶች በቤት ውስጥ ጥቃት ክስ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው ፖሊስ ምርመራ ሲያደርግ የቆየው።
ክሱ ከቀረበ በኋላ አንቶኒ በብራዚልም ሆነ በእንግሊዝ ፖሊስ ቁጥጥር ስር ያለዋለ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላ ያለምንም ክስ ወይም ተጠያቂነት ምርመራው መዘጋቱን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፖሊስ ይፋ ባደረገው መግለጫ ተጫዋቹ የቀረበበትን ውንጀላ ሊያረጋግጥ የሚችል ምንም አይነት መረጃ በምርመራየ አላገኝሁም ብሏል።
የተጫዋቹ ጠበቃ ፖሊስ ሲያደርገው የነበረው ምርመራ የደንበኛየን ንጹህነት ሊያረጋግጥ እንደሚችል እርገጠኞች ነበረን ሲል ተናግሯል።
ፖሊስ ምንም እንኳን ምርመራውን ቢያቋረጥም ጉዳዩ ሙሉ ለሙሉ ከህግ አካላት እጅ እንዳልወጣ ተሰምቷል።
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱ አቃቤ ህግ ቢሮ ሌላ ገለልተኛ ምርመራ ለማስደረግ መዝገቡን በማጣራት ላይ ይገኛሉ ነው የተባለው።
የ2023 የውድድር ዘመን ካበቃ በኋላ ተጫዋቹ በእረፍት ላይ በነበረበት ጋብሬላ ካቫሊን የተባለች የቀድሞ ፍቅረኛው ነበረች ክስ የመሰረተችው ቀጥሎም ሁለት ሌሎች ሴቶች በተመሳሳይ በአንቶኒ የቤት ውስጥ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለፖሊስ ሪፖርት አድርገዋል።
አንድኛው ውንጀላ ተፈጽሟል የተባለው በማንችስተር በሚገኝ ሆቴል ውስጥ መሆኑን ተከትሎ የማንችስተር ከተማ ፖሊስ የራሱን ምርመራ እያደረገ ይገኛል።
የክለቡ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ አንቶኒ ላይ የቀረበበት ውንጀላ የፈጠረበት ተጽእኖ አቋሙን እንዳወረደው ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።
በ2022 ማንችስተርን የተቀላቀለው አንቶኒ ለቡድኑ በውድ ዋጋ በመፈረም ሁለተኛው ተጫዋች ነው፡፡ ዩናይትድ ተጫዋቹን ከአያክስ ለማዘዋወር 82 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ አድርጓል።